
ሁመራ: ሚያዚያ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የወሰን እና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ከአባላቱ እና ከመሪዎች ጋር ውይይት አካሂዷል። በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው “ለነጻነታችን እና ለማንነታችን ያደረግነው እና እያደረግነው ያለው ትግል ፍጹም ሕጋዊ ነው” ብለዋል።
ትግሉ ረዥም እና አስቸጋሪ ዘመናትን አልፎ እዚህ መድረሱን ያወሱት አሥተዳዳሪው “ያልተቋረጠ የትውልድ ቅብብሎሽ ውጤት የዛሬውን ነጻነት አጎናጽፎናል” ብለዋል። የዚህ ዘመን ትውልድም የአባቶቹን የትግል ችቦ ተረክቦ ዳር ለማድረስ ቁርጠኛ መኾኑንም አድንቀዋል።
ነጻነቱ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት፤ ብዙ ውጣ ውረዶች የታለፉበት ነው፤ ካለፉት ዘመናት የትግል ሂደትም ብዙ ትምህርት የተገኘበት ነው ብለዋል። እነዚህን ልምዶች እና ትምህርቶችን በማቀናጀት የማንነቱን ጉዳይ ዳር ማድረስ የሁሉም ኀላፊነት እንደኾነ አስገንዝበዋል። ሃይማኖት፣ ጾታ እና የአመለካከት ልዩነት ያልገደበው አማራዊ ትብብር አስፈላጊ ነው ያሉት አቶ አሸተ በአንድነት ለማንነታችን መቆም ዘመኑ የሚጠይቀው ግዴታ ነው ብለዋል።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ሀቀኛ እና ፍትሐዊ ጉዳይ ይዞ ከሚጠይቀው ሕዝባችን ጎን እንደኾነ ይሰማናል ነው ያሉት። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ዓላማ ግልጽ ነው ያሉት ደግሞ በመድረኩ የተገኙት የጎንደር ልማት እና ሰላም ማኅበር ቦርድ ሠብሣቢ እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር ኢንጂነር
በሪሁን ካሳው ናቸው። ይሄም ዓላማ በነጻነት፣ በእኩልነት እና በፍትሕ የመኖር ነው ብለዋል።
የሕዝቡ ጥያቄ እና የዘመናት ትግል ታሪኩን፣ ባሕሉን፣ እሴቱን እና በአጠቃላይ ማንነቱን ለማስከበር የተደረገ እና እየተደረገ ያለ ትግል መኾኑን ገልጸዋል። እኛ አማራ ነን ስንል በኢትዮጵያዊነታችን እየተደራደርን አይደለም ያሉት ኢንጂነር በሪሁን እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነታችን ተከብሮ መኖር እንፈልጋለን ነው ያሉት።
ሕዝቡ በአካባቢው እና በእርስቱ ተከብሮ የመኖር መብት ያለው መኾኑን ገልጸዋል። በሀገር ልማት እኩል በመሳተፍ ሕገ መንግሥታዊ መብትን ማንም ሊነጥቀው እንደማይችል ጠቁመዋል። የወሰን እና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴው ምክትል ሠብሣቢ ጌጤ አዳል “ትናንት ጥቂት ኾነን ጀምረን ዛሬ ብዙዎች በመኾን ለነጻነታችን የድል ቀን ደርሰናል” ብለዋል።
ሕዝቡ ነጻነት በአገኘባቸው ዓመታት እፎይታ አግኝቶ ማንነቱን በነጻነት እየገለጸ መኾኑንም አስረድተዋል። በውድ ዋጋ የተገኘውን ነጻነት ለማጽናት እና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ለማድረግ ኮሚቴው እና መላ ሕዝቡ በቅንጅት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል። በነጻነት እና ማንነት ትግላችን በርካታ ውጣ ውረዶች ቢገጥሙንም ከአባቶቻችን በወረስነው ጽናት እያለፍናቸው ነው ያሉት ደግሞ የኮሚቴው ኦዲት እና ቁጥጥር ሥራ አሥፈጻሚ ዓባይ ማማይ ናቸው።
ብዙ ታጋይ ጓዶቻችንን አጥተን ነው እዚህ የደረስነው፣ አሁንም ሁኔታው የፈጠረልንን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመን ማንነታችን ሕጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ነው ያሉት። አማራ ነኝ ብለው በየበርሃው የወደቁ ጓዶቻችንን መካስ የምንችለው የሞቱለትን ዓላማ ከዳር ማድረስ ስንችል በመኾኑ ዓላማቸውን ዓላማችን አድርገን በቁርጠኝነት እየሠራን እንገኛለንም ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
