“የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ልዩ ድጋፍ አድርጎልናል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው

17

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም(አሚኮ) “ኑ ጎንደርን እንሞሽር” የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡ በገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩም በርካታ ወገኖች ተሳትፈዋል፡፡ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ጎንደር በርካታ ወርቃማ ዘመናትን አሳልፋለች፤ ከዚያ በኋላ የነበራት ጉዞ ግን ለታሪኳ የሚመጥን አልነበረም ብለዋል፡፡

ለታሪኳ የሚመጥን ሥራ መሥራት እንደሚገባን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የጎንደር አብያተ መንግሥታት ዕድሳት እና የጎንደር የኮሪደር ልማትን ሠርው አሳይተውናል ነው ያሉት፡፡ ከዚህ ሥራ በኋላ የራሳችን ታሪክ ማሳረፍ አለብን የሚለው መነሳሳት መጨመሩን ነው የተናገሩት፡፡ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ለጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት ገንዘብ እያዋጡ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የጎንደር የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በሚቀጥሉት ቀናትም በተከታታይነት እንሠራለን ነው ያሉት፡፡ እስከ ግንቦት 30/2017 ዓ.ም ድረስ የሃብት ማሰባሰብ ሥራው እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡ በጎንደር አለመልማት ይቆጭ የነበረ ሁሉ እንዲሳተፍ እና የራሱን ድርሻ እንዲወጣ የማድረግ ሥራ እንሠራለን ነው ያሉት፡፡

የገቢ ማሰባሰቡ መላ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የእኛ የኢትዮጵያውያን ቀለም ይህ ነው ብለዋል፡፡ ከሶማሌ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ፣ ከኦሮሚያ፣ ከሀረር እና ከሌሎች አካባቢዎች ለጎንደር ልማት ድጋፍ የተደረገበት እንደነበር ነው ያነሱት፡፡ የጎንደር ቀለሟ ይሄ ነው፣ ጎንደር የተሠራቸው በኅብረት ነው፣ አሁን በሕዳሴ ዘመኗ ላይም የጋራ አሻራችንን ያሳረፍንበት ነው ብለዋል፡፡

የቱሪዝም ከተማ የኾነችውን ጎንደርን ከአጼ ቴዎድሮስ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምረን የማሳመር ሥራ እንሠራለን ነው ያሉት፡፡ “የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ልዩ ድጋፍ አድርጎልናል” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በመጀመሪያው ዙር ከፍተኛ ድጋፍ አድርጎልናል፣ አሁንም እንዲቀጥል የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደርን ማመስገን እፈልጋለሁ ነው ያሉት፡፡

በገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩ ያገኘነውን ማሰባሰብ እና አንድነት ለቀጣይ ድሎች መጠቀም አለብን ብለዋል፡፡ የጎንደር አጼ ቴዎድሮስ አውሮፕላን ማረፊያ ላለፉት ዓመታት ያለ ዕድሳት መቆየቱን የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከጎብኝዎች፣ ከተጓዦች እና ከሕዝቡ ቁጥር መጠን አንጻር በቂ አለመኾኑን ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ማረፊያውን ለማደስ ያደረገው ድጋፍ ትልቅ ነው፣ የኾነልን ለእኛ ነው፣ ከአውሮፕላን ማረፊያው በተጨማሪ የኮሪደር ልማት እንደሚሠሩ ቃል ገብተውልናል ነው ያሉት፡፡ ከተማው ብቻ ሳይኾን አውሮፕላን ማረፊያውንም መሥራት አለብን ብለን አየር መንገዱን ስንጠይቀው ፈጣን ምላሽ ሰጥቶናል፤ ለሰጠን ፈጣን መላሽ እናመሰግናለን ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር በመጀመሪያው ዙር የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት ከ382 ሚሊዮን ብር በላይ ማገዙን ገልጸዋል፡፡ ቀሪውን ሥራ ለማጠናቀቅ ደግሞ 121 ሚሊዮን ብር መድበው እንደሚያጠናቅቁ ነው የተናገሩት፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል እና አገልግሎቱን ለማሳለጥ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ።
Next article“ለማንነታችን ያደረግነው እና እያደረግነው ያለው ትግል ሕጋዊ ነው” አቶ አሸተ ደምለው