የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል እና አገልግሎቱን ለማሳለጥ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ።

9

ደብረብርሃን: ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ በበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጻም ግምገማ እና የልምድ ልውውጥ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ እያካሄደ ነው፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የደብረብርሃን ከተማ ጽዱ እና ውብ የጤና ተቋማት እየገነባች መኾኗን ተናግረዋል።

በከተማዋ ያሉት ጤና ተቋማት የሚሰጡትን የአገልግሎት ተደራሽነት እና የሕዝብን እርካታ ከፍ በማድረግ የተሻለ ተሞክሮ እያጎለበቱ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ባለፋት ዘጠኝ ወራት የጤና አመራር ሥርዓትን ለማሻሻል በየደረጃው የሚገኙ የጤና ሙያተኞች እና መሪዎች በማይመች ሁኔታም ውስጥ ኾነው ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ በጤና ተቋማት ዘላቂ የጤና ፋይናስ መገንባት ላይ የተሻለ መነሳሳት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ዘርፉ ከጥገኝነት ተላቅቆ በራስ አቅም የተመሠረተ የጤና አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ማድረስ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ለዚህም ግብ መሳካት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት አንዱ ጉልህ ተግባር መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በክልሉ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት ተደራሽነት አፈጻጸም 80 ነጥብ 1 በመቶ መድረሱንም ጠቁመዋል፡፡

በጤና ተቋማት የመረጃ አያያዝን በማዘመን የዲጅታል አገልግሎት መጀመሩን የተናገሩት ኀላፊው የበለጠ መጠናከር እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡ የግብዓት አቅርቦት እና ሥርጭት ማሻሻልም በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በከተሞችም ይሁን በገጠር ያሉ የሀይጅን እና ሳንቴሽን ተኮር ተግባራት አሁን ካለው የተሻገረ ለውጥ በማስመዝገብ በቀጣይ የበለጠ ሥራ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡

የጤና ዘርፉን በዕውቀት እና በተሻለ ክህሎት መሥራት እና መመራት ስላለበት ያለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1ሺ 500 በላይ መሪዎች ሥልጠና ያገኙበትም ጊዜ ነው ብለዋል፡፡ በመድረኩ ከተለያዩ የክልሉ ዞኖች የተውጣጡ የጤና ዘርፍ የሥራ ኀላፊዎች እየተሳተፉ ነው።

ዘጋቢ፦ ወንዲፍራ ዘውዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ.ር) ከብራዚል እና ሩስያ አቻቸው ጋር ተወያዩ።
Next article“የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ልዩ ድጋፍ አድርጎልናል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው