የገቢ አሠባሠቡን ለማዘመን እየተሠራ ነው።

13

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ እና የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ በገቢ አሠባሠብ አፈጻጸም ላይ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ የኔሰው ማሩ በበጀት ዓመቱ 71 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ እስካሁን ከ42 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ መሠብሠቡን ገልጸዋል።

ከከተማ አገልግሎትም 15 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን መሠብሠቡን ተናግረዋል። የከተማ አገልግሎት ገቢው ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር ብላጫ ቢኖረውም ከዕቅዱ ግን አነስተኛ ነው ብለዋል። ለገቢው ዕድገት እንደምክንያት የቢሮው ተቋማዊ የአቅም ግንባታ ሥራ መሠራቱ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የአሠራር ሥርዓት መሻሻሉ፣ ሥትራቴጂካዊ አጋርነትን እና የሕግ ተገዥነትን የማሳደግ ሥራዎች በመሠራታቸው መኾኑን አብራርተዋል።

ለቅሬታ አቅራቢ ግብር ከፋዮች እና ሌሎች ፈጣን ምላሽ ለሚፈልጉ አገልግሎቶችም አስፈላጊውን ምላሽ መሰጠቱን ገልጸዋል። የገቢ አቅምን ለማወቅ ከጥናት በተጨማሪ አዋጆች እና ደንቦችን የማውጣት እና የመተግበር ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል። ብልሹ አሠራርን በመታገል በኩልም 138 ሙያተኞች በሥነ ምግባር ጉድለት ተጠያቂ መደረጋቸውን ነው ምክትል ኀላፊው የገለጹት።

በቀጣይም ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ገቢን በመሠብሠብ ለልማት ለማዋል ርብርቡ ይቀጥላል ብለዋል። የተቋሙን አሠራር የማዘመን ሥራ እና ሲንታክስ ተጠናክሮ ስለሚቀጥል ግብር ከፋዮች ከአሠራሩ ጋር ለመላመድ እንዲዘጋጁም አሳስበዋል። የከተማ ገቢ አነስተኛነት ለክልሉ ገቢ ማነስ ምክንያት በመኾኑ ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

ደረሰኝን መጠየቅ ሥልጡንነት እና የዜግነት ግዴታን መወጣት ቢኾንም ኅብረተሰቡ ለገዛው እቃ ደረሰኝ በመጠየቅ በኩል የሚቀረው ነገር እንዳለ ነው ያስገነዘቡት። ደረሰኝ እንዲቆረጥም ተባብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ሕጋዊ ነጋዴዎችን እንደምናበረታታ ሁሉ ሕገ ወጦችን ለማስተካከል ተጠያቂ ማድረግም የሥራው አካል መኾኑን አንስተዋል።

የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሱሌማን እሸቱ በበኩላቸው የከተማ አገልግሎት ገቢ የኅብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት የሚሠበሠብ መኾኑን ገልጸዋል። ከተሞች 70 በመቶ የሚኾነውን የመሠረተ ልማት ሥራቸውን በጀት የሚሸፍኑት ራሳቸው ከሠበሠቡት ገቢ መኾን እንዳለበት ሕጉ እንደሚያዝዝ አንስተዋል።

ከማዘጋጃ ቤቶች እና ከከተማ አሥተዳደሮች 22 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ 30 በመቶ እንደተሠበሠበም ገልጸዋል። የጸጥታ ችግር፣ የጥናት ጉድለት፣ ገቢን አሟጦ የመሠብሠብ ችግር ለአፈጻጸሙ አነስተኛነት በምክንያትነት ጠቅሰዋል። በቀጣይ ቀሪ ጊዜ እና በሚቀጥለው ዓመት የከተማ ገቢን በተሻለ ኹኔታ ለመሠብሠብ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

ለዚህም ተቀናጅቶ በመሥራት እና አሠራሮችን በማሻሻል የከተማ አገልግሎት ገቢ አሠባሠብን እንደሚያጠናክሩም አስገንዝበዋል። የሚሠበሠበው ገቢ ለከተሞች ልማት እየዋለ መኾኑን ያነሱት አቶ ሱሌማን የኮሪደር ልማትን እና የስማርት ሲቲ ግንባታን በአብነት ጠቅሰዋል። እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ የተሻለ ገቢ ለመሠብሠብ እንሠራለንም ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኮምቦልቻ ገቡ።
Next articleየውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ.ር) ከብራዚል እና ሩስያ አቻቸው ጋር ተወያዩ።