
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) የላልይበላ ከተማ አስተዳደር ነዋሪው አቶ አበባው አመሬ በከተማው የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ከተቋረጠ አንድ ወር እንደሞላው አስታውቀዋል፡፡ በፈረቃ ሆኖ እንኳ ጊዜውን ጠብቆ በትክክል ተጠቃሚ እየሆኑ እንዳልሆኑና የመቆራረጥ ችግር እንዳለም ገልጸዋል፡፡ እንደ ብረታ ብረት ጣውላ ወፍጮ ቤት የመሳሰሉ የንግድ እና የመንግሥት ተቋማት በሚፈለገው ደረጃ ማኅበረሰቡን እያገለገሉት እንዳልሆነ አንስተዋል፡፡ ከኢኮኖሚያዊ ችግር ባለፈ የዕለት ተዕለት ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይም ተፅዕኖ መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡
የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ነዋሪው አቶ ሀብታሙ መንግሥቴም በተመሳሳይ መብራት መቋረጡ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ መሰናክል እንደፈጠረ አመላክተዋል፡፡ ፈረቃው በትክክል ጊዜውን ጠብቆ ባለመተግበሩ ምክንያት የንግድ ተቋማት ላይ ኪሳራ እያስከተለ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በችግሩ ምክንያት ሆስፒታል ላይ የሰው ሕይወት እያለፈ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ ጨለማን ተገን በማድረግ ስርቆትና ጥቃት ወንጀሎች እንዲበራከቱ ማድረገፉን እንደታዘቡም ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን አላማጣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የነበረው ትራንስፎርመር ሲቀየር ተመሳሳይ አቅም ያለው ትራንስፎርመር እንዳልተቀየረ አስገንዝበዋል፡፡ ነዋሪዎች የተወሰኑ ቀናት በጨለማ ውስጥ በመቆየታቸው ተመሳሳይ አቅም ያለው ትራንስፎርመር በመፈለግ መቅረት ተገቢ ስላልሆነ ለጊዜው አቅሙ ያነሰ ትራንስፎርመር መገጠሙን ነው የተናገሩት፡፡
የተገጠመው ትራንስፎርመር 80 በመቶ አቅም ያለው 20 በመቶ ክፍተት ያለበት መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ ይህ ግን በፈረቃ አገልግሎት ለመስጠት እንቅፋት እንደማይሆን አመላክተዋል፡፡
ተፈላጊ አቅም ያለውን ትራንስፎርመር በጨረታ ሂደቶችን አልፎ ለመግዛት በትንሹ አንድ ዓመት እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡ ሌሎች ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ አቅማቸው ከፍ ያሉ “ትራንስፎርመሮችን” በመጠገን ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ ማድረግ እየተሠራበት ያለ ክንውን ነውም ብለዋል፡፡
በረጅም ጊዜ እቅድ በአካባቢው አንድ ጣቢያ መገንባት እንደሚኖርበት አቶ ሞገስ መኮንን አስታውቀዋል፡፡ ከፈረቃና ከመቆራረጥ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች ግን የክልሉን ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤት መፍታት እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡
ከአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፤ ምላሽ ለማግኘትና ለማቅረብም ጥረታችንን እንቀጥላለን፡፡
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡