ለብርቅዬ እንስሳት የተሰጠው የሕግ ከለላ ምን ድረስ ነው?

29

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ አይነተ ብዙ የተፈጥሮ ውበት ያላቸው ብርቅዬ የዱር እንስሳት ዝርያዎች ባለቤት ናት። ይህ ሀብቷ በሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ በትኩረት ከሠሩበት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ይነገራል። ያለውን ጸጋ በውል ተገንዝቦ ውጤታማ በመኾን ረገድ ሰፊ ክፍተት ያለ ቢኾንም እንዃ ለማለት ነው።

ይህ ሀብት በተገቢው መንገድ እንዲጠበቅ እና እንዲለማ በማድረግ እና ቀጣይነት ያለው ጥቅም መስጠት እንዲችል ማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ ነገር ነው። የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 541/1999 በፌደራል ደረጃ የተደነገገ የዱር እንስሳትን ከማልማት እና ከመጠበቅ አንጻር አላማ ተደርጎ የተደነገገ የሕግ ማዕቀፍ ነው።

አበባው አባይነህ (ዶ.ር) በአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ናቸው። የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ አዋጁ በዱር እንስሳት ዘርፍ ሀብት ያላቸውን አካባቢዎች ማጥናት፣ መከለል እና ማሥተዳደር እንድኹም በዘላቂነት ጥቅም ላይ ማዋልን መሠረት አድርጎ የተደነገገ አዋጅ ነው ይላሉ።

ለዱር እንስሳቶች ከለላ የሚሰጥ እና የሚጠብቅ አዋጅ ነው ብለዋል። በዚህ ዘርፍ የፌደራሉም ኾነ የክልል ሕጎት ነባራዊ ኹኔታውን ባገናዘበ መንገድ ስለ ደህንነታቸው እና ስለ ውጤታማነታቸው የሚጨነቅ አዋጅ ነው ባይ ናቸው። አበባው አባይነህ (ዶ.ር) እንደሚሉት ጥብቅ ስፍራዎች እና ብሔራዊ ፓርኮች ደግሞ ከዋና አዋጁ የሚቀዳ ደንብ ይኖራቸዋል ብለዋል።

በአዋጁ መሠረት በጥብቅ ስፋራው ላይ የወጡ መመሪያዎችን፣ ደንቦችን እና አሠራሮችን የማሥተዳደር ኀላፊነት በዋናነት የዱር እንስሳትን ለሚመለከተው ተቋም የተሰጠ ነው። በጥብቅ ስፍራው ላይ ለእንስሳቱ እና ለጥብቅ ቦታው ደህንነት ሲባል የተከለከሉ ተግባራትን አዋጁ በግልጽ ያስቀመጠ ነው ይላሉ ዶክተር አበባው።

እነዚያ የተከለከሉ ተግባራት እንዳይፈጸሙ ደግሞ እንደየጥብቅ ስፍራው ባህሪ አደረጃጀት ተበጅቶለታል ነው ያሉት። የሚወርዱ አደረጃጀቶችም በጥብቅ ስፍራው ውስጥ ያሉ እንስሳትን ደህንነት የማረጋገጥ እና ሕገ ወጥ ተግባራትን የመጠበቅ ኀላፊነት የተሰጣቸው ናቸው ብለዋል። አዋጁ የተከለከሉ ተግባራትን ያከናወነ አካል ላይ መወሰድ ስላለበት ሕጋዊ እርምጃም ጨምሮ ያስቀመጠ ሕግ እና መመሪያ የተበጀለት እንደኾነም ነው የተናገሩት።

ይህም ሳይፈቀድ ወደ ጥብቅ ስፍራው የጦር መሳሪያ ይዞ መግባት፤ ማደን፣ ማጥመድ፣ በውስጡ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን መቁረጥ፣ መውሰድ፣ መጨፍጨፍ፣ ማበላሸት፣ እሳት ይዞ መገኘት፣ ካልተፈቀደ ቦታ ላይ ማር መቁረጥ፣ እንስሳትን ወደ ቦታው አስገብቶ ማሰማራት፣ ተባይ እና ኬሚካል ይዞ መገኘት፣ ወዘተ የመሳሰሉት በአዋጁ የሚያስጠይቁ እንደኾኑ ተመላክተዋል ነው ያሉት።

ሰዎች ክልከላዎችን ተላልፈው ከተገኙ እንደተፈጸመው ወንጀል ባህሪ እስከ 30 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እና እስከ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣም በአዋጁ በግልጽ ተደንግጓል ብለዋል። የዱር እንስሳት ጥበቃ አዋጁ ላይ ብቻ ሳይኾን በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 91 ጀምሮም ጥበቃ እንዲደረግ፤ ሕዝቡም ለሚደረገው ጥበቃ እንድተባበር እና መንግሥትም ኀላፊነቱን እንዲወጣ ሲል የተቀመጠ ነው ይላሉ ዶክተር አበባው።

በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀጽ 353 ንዑስ አንቀጽ ሦስት(3) ላይም ለዱር እንስሳት እና ለጥብቅ ስፍራዎች በተለይ ለብርቅየ እንስሳት ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው በአጽንኦት ያነሳል ነው ያሉት። እዚሁ የወንጀለኛ ሕጉ ላይ ብርቅዬ እንስሳትን ግድያ የፈጸመ ወይም ይዞ ሲንቀሳቀስ የተገኘ አካል ላይ እስከ 12 ዓመት ጽኑ እስራት እና እስከ 100 ሺህ ብር ድረስ እንደሚያስቀጣ በግልጽ የተቀመጠ ነው ይላሉ።

አዋጅ ቁጥር 541/1999 የዱር እንስሳትን ከመጠበቅ እና ከለላ ከመኾን አንጻር የወጣ ቢኾንም እንኳ የተፈጻሚነት ወሰኑ አነስተኛ እንደኾነ ዶክተር አበባው በአጽንኦት አንስተዋል። ለዚህም በተለያዩ አካባቢዎች በብርቅየ እንስሳት እና በጥብቅ ስፍራዎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎች ማሳያዎች ናቸው ይላሉ።
በማኅበረሰቡ እና በፍትሕ አካላቱ ላይ ያለው የግንዛቤ አድማስ ገና መስፍት ያለበት እንደኾነም አንስተዋል።

ከዚህ በፊት በዘርፍ ላይ ወንጀል ፈጽመው የተገኙ አካላት ተገቢውን የሕግ እርምጃ ሳይሰጣቸው በቀላል መቀጮ የተለቀቁበትን አጋጣሚም አውስተዋል። ይህ መኾኑ ማኅበረሰቡ ለጉዳዩ ትኩረት እንዳይሰጠው የሚያደርግ ተግባር ነው ይላሉ። ተገቢ እና አስተማሪ ያልኾኑ ውሳኔዎች ሕገ ወጦችን ያበረታታሉ ነው ያሉት።

አንድ ወንጀል ፈጻሚ የተቀጣው ቅጣት እሱን ከማስተማር ይልቅ ትርፍ የሚያገኝበት ከኾነ መቀጠሉን አያቆምም ሌሎችም ከሱ አይማሩም ብለዋል። ከዚህ በፊት በዚህ ዘርፍ ሲሰጡ የነበሩ የሕግ ውሳኔዎች በሕገ ወጥ ተግባር ላይ የሚሰማሩ አካላትን በዘላቂነት ከማስተማር አንጻር ችግር የነበረባቸው እንደነበሩም አስታውሰዋል።

አዋጅ ወረቀት ላይ ያለ ነገር ነው፤ ትርጉም የሚኖረው ደግሞ በተግባር ሲተረጎም ነው ይላሉ ዶክተር አበባው። የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ አዋጁም መሬት ላይ ለውጥ እንዲያመጣ በተግባር መተርግም አለበት ብለዋል። ሕግ አውጭው፣ ፈጻሚው እና አሥፈጻሚው አካል ወደ መሬት ማውረድ እና ማስተግበር አለባቸው ነው ያሉት። ያ ካልኾነ ግን አዋጁ ብቻውን ጥርስ አይኖረውም ብለዋል። ጥብቅ ስፍራዎች በአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ብቻ ውጤት አያመጡም ብለዋል። ይልቁንም በየዘርፍ ያለ አካል ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ እንደኾነም ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡም ከዕለት ጥቅም ይልቅ ዘላቂ ጥቅም አገኛለሁ ብሎ እንዲያስብ ግንዛቤውን ማሳደግ ያስፈልጋል ነው ያሉት። በዘርፍ ሕገ ወጥ ተግባር የፈጸመ አካል እውነትም ሕጉን መሠረት አድርጎ 30 ሺህ ብር እና በአምስት ዓመት ጽኑ እስራት ቢቀጣ ተመልሶ ወደ ተግባሩ አይሰለፍም ነው ያሉት።

መሬት ላይ ግን ይህ በትክክል እየኾነ አይደለም ብለዋል። ብርቅዬ እንስሳትን የገደለ አካልን ሕጉን መሠረት ተደርጎ እስከ 100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እና እስከ 12 ዓመት ጽኑ እስራት ቢቀጣ ግለሰቡም አይደግመውም ሌላውም ከሱ ይማራል ነው ያሉት።

ከሰሞኑ በስሜን ተራራዎች ላይ የተፈጸመው ዋልያዎችን አድኖ የመግደል ተግባር መወገዝ ያለበት ነው ብለዋል። የኢትዮጵያን ምልክት የማጥፋት ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው እንደኾነም ገልጸዋል። በቀጣይም ጥብቅ ከለላ ማድረግ እና ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መኾኑን ማወቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትም ተገቢውን እርምጃ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ የፍትሕ አካሉ ትልቅ ሥራ ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

በፓርኩ ዙሪያ ያለው ማኅበረሰብም ከዝምታ ወጥቶ ባለቤትነቱን ማሳየት አለበት ብለዋል። ሕገ ወጦችን መከላከል እና መምከር ይኖርባቸዋል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ መገንዘብ ያለበት ጥብቅ ስፍራን መጠበቅ፤ ተፈጥሮን መጠበቅ በተዘዋዋሪ ህልውናን መጠበቅ መኾኑን ማስገንዘብም ያስፈልጋል ነው ያሉት። በስሜን ተራራዎች ዙሪያ ያለ ማኅበረሰብ ተፈጥሮው ባይኖር በዘላቂነት መኖር እንደማይችል ማስተማር እና ማሳወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

ተፈጥሮ ካለ ሰው ይኖራል። ተፈጥሮ ከወደመ ሰው አይኖርም የሚለው መላምት ሳይኾን እውነት መኾኑንም ዶክተር አበባው አስገንዝበዋል። መታወቅ ያለበት ጉና ተራራ ባይኖር ታችኛው ማኅበረሰብ ቀርቶ ጉና ላይ ያሉ ማኅበረሰቦች እንኳ ውኃ የማያገኙ መኾኑን ማወቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በመጨረሻም ሰው እና ተፈጥሮ በተደጋግፎ የሚኖሩ በመኾናቸው ለተፈጥሮ እና በውስጡ ላሉ ብዝኀ ሕይወት ትርጉም መስጠት ይኖርብናል እንላለን።

በሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“አባቶቻችን የሠሩትን ቅርስ ማደስ ብቻ ሳይኾን የዕድገት ሕልማቸውንም ዕውን ለማድረግ እየሠራን ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኮምቦልቻ ገቡ።