
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ኑ ጎንደርን እንሞሽር” በሚል መሪ መልዕክት ለታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ዘርፈ ብዙ ልማት የሚውል የገቢ ማሠባሠቢያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል እየተካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የሶማሌ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሙስጦፋ ሙሁመድ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ እንዲሁም ሚኒስትሮች፣ የክልል እና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ መሪዎች፣ ባለሃብቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በሀገራችን የከተማነት ታሪክ ውስጥ ከክትመት እስከ ኪነ ጥበብ፣ እንዲሁም በሥልጡንነት ረገድ ጎንደር ለብዙ ከተሞች ምሳሌ ናት ብለዋል። ጎንደር የኢትዮጵያውያን ሁሉ የታሪካችን አሻራ እና የማንነታችን መገለጫ ናት ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ይሁን እንጅ ልማት ተነፍጓት ባለችበት የመቆም እጣፋንታ ገጥሟት፤ ቅርሶቿም ተጎሳቁለው እና የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸው ቆይታለች ብለዋል።
በዚህም የተነሳ ነዋሪዎቿ በቅሬታ እና ከተማዋ በድባቴ ውስጥ ስለመቆየታቸውም ጠቁመዋል። ካለፋት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን አቧራውን አራግፈን ጎንደር ያላትን እምቅ የመበልጸግ ዕድል መጠቀም ጀምረናል ነው ያሉት። ድምቀቷ የበለጠ እንዲታይም ጅምር ሥራዎችን አከናውነናል ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።
የነዋሪዎቿ የደስታ እና የተስፋ መጠን ለከተማዋ ከተደረገው እና ከኾነው በላይ ኾኖ አግኝተነዋል፤ በተሠሩ ጅምር ሥራዎች የሕዝቡን በጎ ምላሽ አይተናል፤ የበለጠ ውብ የማድረግ ሃሳብን እንድናውጠነጥንም የነዋሪዎች አደራ አስገድዶናል ብለዋል። ለትውልድ የምናስረክባትን ውብ እና ማራኪ ከተማ ለመገንባት ቆርጠን ተነስተናል፤ ይህንን ለማድረግ ጊዜው አሁን እና ዛሬ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ያለንበት ጊዜ የጎንደርን የቀደመ ታላቅነት ለመመለስ ብቻ ሳይኾን አዳዲስ ስፋት እና ጥራት ያላቸውን ልማቶች በመገንባት ለትውልድ ለማስረከብ የምንሠራበት ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ። አባቶቻችን ውብ አድርገው የሰጡንን፣ እስካሁን ግን አቧራ ለብሳ የቆየችውን ከተማ ውብ እና ማራኪ አድርጎ የመገንባቱን ኀላፊነት ወስደናል ሲሉም ገልጸዋል።
ለጎንደር አንድም ያለፈ ቅርስ እና ሀብቷን የማደስ እና የመጠበቅ፣ ሁለትም አዳዲስ ልማቶችን የመሥራት ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት። ርእሰ መሥተዳድሩ “ጎንደር ሕንጻ ብቻ አይደለም የተሸከመችው፤ ይልቁንም የማንነታችን መገለጫ አሻራዎቻችንን አምቃ ነው የያዘችው” ብለዋል። የጎንደር እና የኢትዮጵያም መገለጫ የኾነውን የአጼ ፋሲል አብያተ መንግሥት ታሪክ እና ክብሩን በመጠነ መልኩ መጠገን ስለመቻሉም ጠቅሰዋል።
በጎንደር ከተማ ውስጥ ተጀምረው በመጓተት ላይ የነበሩ መሠረተ ልማቶችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን(ዶ.ር) ጨምሮ ሁሉም መሪዎች በልዩነት በመከታተል እንዲጠናቀቁ እየተሠራ ነው ብለዋል። ጎንደርን ከቆየው ችግሯ ለማላቀቅ፣ የቱሪዝም መናኻሪያም ለማድረግ በትኩረት ይሠራል ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ። በመተባበር እንሠራለን፤ ጎንደርን የተነቃቃች የባሕል እና የቱሪዝም እምብርት እናደርጋታለን ሲሉም ተናግረዋል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ።
የጎንደርን የታሪክ አሻራ ለማደስ የጎንደርን ጥሪ ተቀብለናል፤ የአባቶቻችንን ቅርስ ማደስ ብቻ ሳይኾን የዕድገት ሕልማቸውን እውን ለማድረግም እንሠራለን ነው ያሉት።
የጎንደርን የሙሽርነት ጥሪ ወደሚጨበጥ የጉልበት እና የቁስ ሀብት ቀይረን የቀደመውን የአባቶቻችንን ሥራ እናድሳለን፤ የወደፊቱን ትውልድም መዳረሻ ከአሁኑ እናስተሳስራለን ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የጎንደርን ቅርስ ጠግነው የመልማትን አቅጣጫ አሳይተውናል፤ ጎንደር ተጨማሪ ልማት ያስፈልጋታል የሚል ማንኛውም ዜጋ የጎንደርን ጥሪ መቀበል እና በዚህ ንቅናቄ በመሳተፍ አሻራውን ማስቀመጥ ይገባዋል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
