
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ኑ ጎንደርን እንሞሽር” የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል። በመርሐ ግብሩ ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የሶማሌ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሙስጦፋ ሙሐመድ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ ሚኒስትሮች፣ የክልል እና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ መሪዎች፣ ባለሃብቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ መርሐ ግብሩ የሚያስገርም ድጋፍ ያገኘንበት ነው ብለዋል። ከችግሮቻችን ለመውጣት እና ለመሻገር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጋችሁልናል ነው ያሉት። ቃል የተገባው ገንዘብ ትልቅ ከመኾኑ ባሻገር የበለጠ አንድነታችንን እና አብሮነታችንን ያሳየንበት ምሽት ነው ብለዋል።
መርሐ ግብሩን ላዘጋጁ እና ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በመካከላችሁ የቆምኩት ማዕከላችሁ እና ትኩረታችሁ በሙሉ ልማት እና ልማት ብቻ የኾነውን እናንተ ኢትዮጵያውያንን ለማመስገን ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማት ትልቅ ሃሳብ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ሃብትን፣ ሃሳብን፣ ዕድገትን እና ዘመንን ማስተሳሰር ነው፣ ከተሞች የዕድገት መሠረቶች ናቸውና ነው ያሉት።
ከተሞች ሲያድጉ የሕዝብን ኑሮ ያሻሽላሉ፣ አስተሳሰብን ያሰፋሉ፣ ሥልጣኔንም ይዋጃሉ፣ የበለጠ ዕድገት ይኖር ዘንድ መስፈንጠሪያ ይኾናሉ ብለዋል። ለኢትዮጵያ ከተሞች ምርጫቸው ሁለት ነገር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ አንደኛው በዕውቀት እና በሃብት ማደግ፣ ከዓለም የሥልጣኔ ጉዞ ጋር መሠለፍ እና ሰልፍን ማሳመር፤ ሁለተኛው ከእነ ቡትቷችን ለዘላለም በአረጀ ብሒል ሰጥሞ መናኛ ከተማ መኾን ነው ብለዋል።
ሁለተኛው ምርጫ እንደማይመረጥም አመላክተዋል። ሁለተኛውን ምርጫ ለመምረጥ የከጀሉ ቢኖሩም ዘመን አይፈቅድም ነው ያሉት። ሠልፍን ማሳመር፣ ወደፊት መትጋት የከተሞቻችን ብሒል መኾን አለበት ብለዋል። የኢትዮጵያ ከተሞች እጣ ፈንታቸው መሠልጠን እና መሠልጠን መኾኑንም ተናግረዋል።
የዓድዋ ድል መታሰቢያን በሚያስደንቅ ሁኔታ መገንባት የይቻላል መንፈስን የሰጠ መኾኑንም ገልጸዋል። ዕውቀት፣ ሃብት፣ ሰው እና ብሩህነት ከተስማሙ ኢትዮጵያን ማስፈንጠር ይቻላል ነው ያሉት። በብልሕነት፣ በመገለጥ ስሜት አዲስ ሃሳቦችን በማማተር፣ ሕዝብን አስተባብሮ መሥራት ነው የዕድገት ምንጩ ብለዋል።
ኢትዮጵያን እንዴት እናሳድጋት የሚለውን እንቆቅልሽ ለመፍታት ቁልፉን የያዝነው ይመስለኛል ነው ያሉት። ባለው እየገነቡ፣ እየጨመሩ የሚሄዱ ሁሉ ተግባራቸው ሕያው መኾኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ኃያል ሀገር ናት ያሉት ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ እኛ በሰፋነው የአስተሳሰብ ምሕዳር ብቻ የምትገለጽ አይደለችም፣ ኢትዮጵያን ከእኛ በላይ ሌሎች ከፍ ሲያደርጓት በዚያ ልኬታ ይሄ ትውልድ የሚጠበቅበትን መከወን ይኖርበታል ነው ያሉት።
ስለ ኢትዮጵያ ዘክረው፣ ተናግረው የማይጠግቡ አያሌ ሕዝቦች አሉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ እነሱ ባዩን እና በተመለከቱን ልኬታ ራሳችንን ብናይ እንዴት ያለ ጸጋ ነው እላለሁ ብለዋል። የኢትዮጵያ ኃያልነት ታሪኳ ብቻ አይደለም፣ የኢትዮጵያ ኃያልነት መሠረቱ ሕዝቦቿ ሀገር መውደዳቸው ነው፣ በተስረከረከ ጊዜያዊ የኢትዮጵያ እሳቤ የሚጓዙ አዲስ ፍጡራን አይደሉም፣ ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተሞከሩ ስርክርክ ሃሳቦችን ማሸነፍ ችላለች፣ መቀጠል ችላለች፣ ሳንካ ያጋጠማቸው ሀገራት ለመሻገር ሲውተረተሩ ይታያሉ፣ የኢትዮጵያውያን ግን ይሄን አይፈቅዱም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያዊነት ኃያልነት በመኾኑ ይሄን አጥብቆ መቀጠል የተገባ መኾኑን ነው ያመላክቱት። “ጎንደር የኢትዮጵያውያን የጋራ የእጅ ሥራ ናት፣ ይህ አዘቦታዊ ንግግር አይደለም፣ ጎንደር በጋራ የተገነባች ናት” ነው ያሉት። የጎንደር አብያተ መንግሥት ከተገነቡ እስከ ግንቡ ጠባቂዎች ብዙ ኢትዮጵያውያን ተመላልሰዋል፣ ግንብ መጠበቅ ይቻላል፣ ይህ ትውልድ ግን ይሄን የመረጠ አይመስለኝም፣ መጠበቅ አንድ ነገር ነው፣ በላይ ላይ ይናዳል፣ ዘመን ሲሸብት፣ ሲጫነው መፍረስ ይጀምራል፣ ከመፍረስ ለማዳን ብሩህነትን እና መወሰንን ይጠይቃል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለወሰዱት ወሳኝ እርምጃ ምስጋና አቀርብላቸዋለሁ ነው ያሉት። የጎንደር ሠፈሮች መጠሪያ ሁሉ ኢትዮጵያዊ መጠሪያ ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ከጃን ተከል እስከ አባ ጃሌ፣ ከሸዋኔት እስከ ደራ፣ ከወገሎ እስከ ሳሙና በር፣ ሁሉንም መሠረት ያደረጉ የወንዝ እና የተራራ ስሞቿ የኢትዮጵያዊነት ኅብረት ናቸው ብለዋል።
ሥነ ጥበቡ፣ ኪነ ሕንጻው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሥሪት ነው፣ ጎንደርን የግዴታ የልማት ማዕከል ማድረግ ተገቢ ይኾናል ነው ያሉት። የልማት ማዕከል ማድረግ ማለት ሕዝብን ከድህነት ማውጣት ማለት ነው፣ ቁልፉ ይሄ ነው ብለዋል። እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ከተሞች በትውልድ ቅብብሎሽ መዘመን እና ማደግ ይኖርባቸል ነው ያሉት። የኮሪደር ልማት ሥራዎች የተሐድሶ ዘመን ዋነኛ ካስማ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ይሄን ማስፋፋት እና ማጠናከር ይኖርብናል ነው ያሉት።
የጎንደር ገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እንዲሳኩ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። የጎንደር ልማት የበለጠ እንዲሠፋ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ አመስግነዋል። ለጎንደር ያልኾነ ለምን ይኾናል? ያሉት ፕሬዝዳንቱ በልማት ጎዳና ከሄድን ሰላማችን ይጸናል፣ ሰላማችን ካጸናን አስተውሎታችን ሁሉ ይሰፋል ይዳብራል ነው ያሉት።
ነውጥ የሚያንሰላስል ሰላም የለውም፣ የዕድገትም እንቅፋት ነው፣ ጎንደር እና አካባቢው ለብዙ ዘመን በዚህ መሰል ተግባር ታውኳል፣ ፍቱን መዳኃኒቱ ግን ልማት በመኾኑ አስተዋይ እና አርቆ አሳቢ በመኾን ሰላምን አዳብረን፣ ከዓለም ፊት በክብር መቆም አለብን ነው ብለዋል።
ለዘላለም ኋላቀር መባል አታካች እና አድካሚ መኾኑንም ገልጸዋል። በአንባጓሯችን ልኬታ የምንመዘን ሳይኾን በልማት አጋዥነታችን የምንለካ መኾን ይኖርብናል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ዕድለኛ ናት፣ ጽኑ መሪዎች አሏት፣ ተስፋችንም የጸና ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
