“መንግሥት በክልሉ ሰላምን ለማስፈን ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ውጤታማ ሥራ አከናውኗል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

25

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፥ የክልሉን ወቅታዊ የሰላምና የልማት ጉዳዮች አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በክልሉ ተፈጥረው የነበሩ የሰላምና የጸጥታ ችግሮች በዋናነት ከፖለቲካዊ ጽንፈኝነት ጋር የተያያዙ እንደሆኑ አስታውሰዋል። በወቅቱ መሪዎች በሚጠበቅባቸው ልክ ችግሩን ታግለው በማስተካከል ረገድ ለዘብተኛ አቋም መውሰዳቸውን ተናግረዋል። በዚህም ጽንፈኛ ቡድኖች በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት በክልሉ ሰላምን በማስፈን ረገድ ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ውጤታማ ሥራ ማከናወኑንም ተናግረዋል። የክልሉ ነዋሪዎችም የጽንፈኛ ቡድኑን ትክክለኛ ማንነት ተገንዝበው ከመንግስት ጎን በመሆን ለዘላቂ ሰላም የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ክልሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በተሻለ የሰላምና የልማት ጉዞ ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል። በክልሉ የተገኘውን ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ በመንግሥት በኩል ሁለት የመፍትሔ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን አስረድተዋል። የመጀመሪያው ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በዚህ ረገድ መንግሥት ዘወትር ለሰላም በሩን ክፍት አድርጎ እየሠራ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል የቀረበውን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን በመተው የክልሉን ሰላም ለማወክ በሚሰሩ ጽንፈኛ ቡድኖች ላይ መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚቀጥል አመላክተዋል። ኢዜአ እንደዘገበው የአማራ ክልል ሕዝብ በቀጣይ ሰላምን በማስጠበቅ በኩል ከመንግሥት ጎን በመሆን የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበበዓል የታየው ዋጋን የማረጋጋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
Next article“ጎንደር የኢትዮጵያውያን የጋራ የእጅ ሥራ ውጤት ናት” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ