በበዓል የታየው ዋጋን የማረጋጋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

24

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ በትንሳኤ በዓል ምክንያት የሸቀጦች ዋጋ እንዳይንር ለመሥራት ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን መግለጫ ሰጥቶ ነበር። አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዲጂታል ሚዲያም ከበዓል ማግሥት የበዓል ዋጋ እንዴት እንደነበር ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

የባሕር ዳር ነዋሪዋ ወይዘሮ ታንጉት ሙጬ ዘይት እና ዱቄት በበዓል ምክንያት እንዳልጨመረ ገልጸዋል። ዶሮ ቀድሞውንም ዋጋው ውድ ኾኗል፣ በፋሲካው ግን አለመጨመሩን ተናግረዋል። ስጋት ቢያድርባቸውም የበዓል ዋጋ የተረጋጋ በመኾኑ ”ተመስገን ነው” ብለዋል። ”ዘንድሮ የበሬ ዋጋ ቢጨምርም እንደሰጋሁት ዋጋ አልተቆለለም” ያሉት ደግሞ አቶ ታምራት ቢክስ ናቸው። በአንጻሩ የበግ እና ፍየል ዋጋ ያልተጋነነ መኾኑንም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አትክልት አሳቤ ቢሯቸው በየደረጃው እና ከአጋር አካላት ጋር ዋጋን ለማረጋጋት የሠራውን ሥራ አብራርተውልናል። በትንሳኤ በዓል ዋጋን ለማረጋጋት በእቅድ መሠራቱን የገለጹት ምክትል ኀላፊዋ በሁሉም የክልሉ ቀጠናዎች ባለሙያ በማሰማራት ምርት እና ገበያን ለማጣጣም እና ሕገ ወጥነትን ለመከላከልም መሠራቱን ነው ያብራሩት።

በምርት አቅርቦት፣ የግብይት ማዕከላትን በማመቻቸት እና ሕገ ወጥን በመቆጣጠር ገበያ የማረጋጋት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡ ጊዜያዊ የመገበያያ ቦታዎች በመፍጠር የሰብል፣ የፋብሪካ እና የእንስሳት ምርቶች ወደ ገበያ እንዲወጡ መሠራቱን ተናግረዋል። የእንቁላል እና የዶሮ ጊዜያዊ መገበያያዎች መዘጋጀታቸውን የጠቀሱት ወይዘሮ አትክልት አምራች ኢንተርፕራይዞችም ወደ ግብይት ማዕከሉ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል።

የሥጋ ኮሪደሮችም ተዘጋጅተው በኅብረት ሥራ ማኅበራት እና በሌሎች አማራጮችም የሥጋ ቅርጫ ለኅብረተሰቡ ቀርቧል ያሉት ምክትል ኀላፊዋ ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን፣ ደብረብርሃን፣ ኮምቦልቻ እና ደሴ ከተሞችን በአብነት ጠቅሰዋል። ወተት በአምራቾች እና በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል መቅረቡንም አንስተዋል።

በሕገ ወጥ የምርት ዝውውር ላይ ቁጥጥር በማድረግም በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና በወልድያ ከተማ አሥተዳደር ነዳጅን በደበቁ፣ እና ሽንኩርትን እና የምግብ ዘይትን በሕገ ወጥ ሲያዘዋዉሩ በተገኙ ላይ እርምጃ መወሰዱን አንስተዋል። በሥራው ላይ ከሕዝብ በተሰበሰበ ግብረ መልስ የዋጋ ማረጋጋቱን እንዲቀጥል መጠየቁን ያነሱት ወይዘሮ አትክልት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ወልድያ ከተማ አሥተዳደር እስከ ሰኔ ድረስ የግብይት ሰንሰለት አዘጋጅቶ እየሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል። ጎንደር እና ደብረ ማርቆስ ደግሞ ባዛር እያዘጋጁ እና ግብይትን እያመቻቹ ነው ብለዋል። በነጻ ገበያ ሥርዓቱ የተደረገውን ግብይት ሳይጨምር እስካሁን 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል እና የፋብሪካ ምርት እንዲኹም 11 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት እና ፈሳሽ ሳሙና አስተሳስረናል ነው ያሉት።

ይህ በመሠራቱም ዋጋን ማረጋጋት መቻሉን ነው ምክትል ኀላፊዋ የገለጹት። ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል። በተለይም አምራችና ሸማችን የሚያገናኙ የግብይት ማዕከላትን በማስፋፋት የግብርና ምርትን ቀጥታ ለሸማቹ እንዲደርስ የድንኳን ግብይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለጹት።

ቢሮው የሸቀጦችን ዋጋ ለማረጋጋት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ለኑሮ ውድነት እና ዋጋ መናር ዘላቂ መፍትሄው ምርትን ማሳደግ መኾኑን የገለጹት ወይዘሮ አትክልት ከከተማ ግብርና ጀምሮ ምርትን ለማሳደግ መሠራት አለበት ነው ያሉት። የሌማት ትሩፋት ኑሮን በማረጋጋት አስተዋጽኦ ስላላቸው እነሱ ላይ መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የምርት ነጻ እንቅስቃሴ አለመኖር በአቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይህም ለዋጋ መናር ምክንያት ስለኾነ ሁሉም ለዘላቂ ሰላም መሥራት አለበት ነው ያሉት። ሕገ ወጥ ንግድን ማጋለጥ እና ለሚመለከተው አካል መረጃ በመስጠት ተባብሮ መሥራት የችግሩ ሌላው መከላከያ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበሰሜን ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ ሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል።
Next article“መንግሥት በክልሉ ሰላምን ለማስፈን ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ውጤታማ ሥራ አከናውኗል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ