በሰሜን ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ ሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል።

30

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በወቅቱ በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር ዘርፍ አሥተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ(ዶ.ር) መርዓዊና ሜጫ ለዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ማስፋፊያነት በክልሉ እንደ ዐይን ብሌን የምንሳሳለት አካባቢ ነው ብለዋል።

ነገር ግን በርካታ በጀት የፈሰሰባቸው ፕሮጀክቶች የወደሙ ከመኾኑም ባሻገር ታሪክን እያበላሸን ነው ብለዋል። በሀሳብ የበላይነት ማመን ሲቻል በጠብመንጃ፣ ሰውን በመግደልና በተዛባ አመለካከት ለውጥ ሊመጣ አይችልም፤ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ እሴቶችም ተሸርሽረዋል ብለዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን መርዓዊ ከተማ የብዙ ከተሞች ተምሳሌትና የተሞክሮ ማዕከል የነበረች መኾኗን አንስተዋል። አሁን ግን የመንግሥት ሠራተኞች፣ ኑዋሪው፣ መምህራን፣ ህፃናት እና እናቶች የሚገደሉበት የደም ምድር ኾኗል ማለታቸውን ከአማራ ብልጽግና የተገኘ መረጃ ይጠቁማል።

በተጨማሪም የመንግሥት ተቋማትና መሰረተ ልማት የወደመበት ስለኾነ ዛሬ የተገኛችሁ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላችሁን ኃላፊነት ልትወጡ ይገባል ብለዋል።

የምሥራቅ እዝ 302ኛ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል መለስ መንግስቴ በበኩላቸው ከግል ጥቅምና ፍላጎት በመፅዳት ስለሰላም በመምከር የችግሩም ኾነ የመፍትሔው አካል በመኾን ለማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ሲባል ጫካ የገቡ አካላት ከመንግሥት ጎን መቆም ይችሉ ዘንድ ማኅበረሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ አሳስበዋል ።

ተሳታፊ አስተያየት ሰጪዎችም ከወሬ ባለፈ በተግባር መንግሥት ለሰላም መረጋገጥ በሩን ክፍት ከማድረግ በተጨማሪ በከተማው ያሉትን የመልካም አሥተዳደር እና የአሠራር ሥርዓት ክፍተትን መለየት እና ማረም ያስፈልጋል ብለዋል ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article8 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 151 አልሚ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን የሰሜን ወሎ ዞን አስታወቀ።
Next articleበበዓል የታየው ዋጋን የማረጋጋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።