
ወልድያ:ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” በሚል መሪ መልዕክት የሰሜን ወሎ ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ያዘጋጀው ዞናዊ የማጠቃለያ መርሐግብር በቆቦ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ማደግ የቴክኖሎጅ ሽግግር ያመጣል፤ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረትንም ይቀርፋል ብለዋል። ለሀገሪቱ ዕድገትም ወሳኝ መኾኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ከአንድ ሺህ በላይ አልሚ ባለሀብቶች ፈቃድ አውጥተው እንዲሠሩ መደረጉንም ገልጸዋል። ነገር ግን ከአጋር አካላት የቅንጅትጉድለት፣ ከባለሀብቶች የአፈጻጸም ችግሮች፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዞኑ ከተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ጋር ተደማምረው ወደ ተጨባጭ ምርት አልተገባም ብለዋል።
በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በ2013 እስከ 2014 ዓ.ም ብቻ 197 ፕሮክቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በዘርፉ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞችም ከሥራቸው ተፈናቅለዋል ነው ያሉት።
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መድረኮችን በሁሉም ወረዳዎች እና ከተሞች ማካሄድ አስፈላጊ ነበር ያሉት አሥተዳዳሪው ባለፉት ሦስት ወራት በወረዳዎች ፕሮጀክቶችን በማስመረቅ እና በመጎብኘት የዞኑ ሥራ አሥፈጻሚ የመራው ትልቅ ንቅናቄ ተፈጥሯል ብለዋል። በርካታ ችግሮችም መቀረፋቸውን ተናግረዋል።
“ኢንቨስትመንት በባሕሪው አስተማማኝ ሰላም ይፈለጋል፤ አስተማማኝ ሰላምን ማጽናት ደግሞ የሁሉም ዜጋ የጋራ ጉዳይ መኾን ይገባዋል” ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው።
ሰላም ላይ የመግባባት፣ በአንድነት ቆሞ ትግል የማድረግ እና ልማትን እያደናቀፈ ያለውን ቡድን በማውገዝ ወደ አስተማማኝ ሰላም የመመለስ ጉዳይ የጋራ ጉዳያችን መኾን ይገባዋል ብለዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ሞላ ደሱ በተለያዩ ምክንያቶች ለዓመታት ምርት አቁመው የነበሩ 12 ኘሮጀክቶች በአዲስ መልክ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።
በተቋማት መካከል የነበረውን መገፋፋት በማስቀረትም በቅንጅት እየሠሩ መኾኑን ነው የገለጹት።
የዞኑ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ዕድገት እያሳየ መጥቷል ያሉት መምሪያ ኀላፊው ባለፉት ዘጠኝ ወራትም 8 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 151 አልሚ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል ብለዋል።
የኢንቨስትመንት መሬት አጥሮ ማስቀመጥ፣ ከተሰጣቸው ዓላማ ውጭ መጠቀም እና የኀይል እና የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት የዘርፉ ፈተናዎች መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
