
ጎንደር: ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለምልምል የፖሊስ አባላቱ የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ በዞኑ እና በጎንደር ከተማ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ገልጸዋል። ይህንን ሰላም ለማጽናት ምልምል የፖሊስ አባላቱ ከማኅበረሰቡ ጋር በመኾን የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስረድተዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር አንተነህ ቴዎድሮስ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች አለመረጋጋቶች ያሉ በመኾናቸው ኅብረተሰቡ የልማት ሥራዎች ላይ እንዲያተኩር ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል። የፖሊስ አባላቱ የከተማዋን ሰላም ለመጠበቅ እና ሰላምን ለማጽናት የሚኖራቸው ሚና የጎላ ነው ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር አየልኝ ታክሎ ናቸው።
ምልምል የፖሊስ አባላቱ በጎንደር ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችንም ተመልክተዋል። በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን መመልከታቸው ሰላምን በማረጋገጥ የልማት ሥራዎች በተገቢው መንገድ እንዲከወኑ ታሳቢ ያደረገ እንደኾነ ተገልጿል።
በከተማው እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ መኾናቸውን ምልምል የፖሊስ አባላቱ ተናግረዋል። ወደ ተመደቡባቸው አካባቢዎችም ሲሄዱ ሙያው በሚፈቅደው መሠረት ሕዝባቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ፦ ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
