ስለኮሌራ በሽታ ማወቅ ያለብን፦

44

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ አሞኜ በላይ በአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ቡድን መሪ ናቸው። የኮሌራ በሽታን በተመለከተ ለአሚኮ ዲጅታል ሙያው ሀሳባቸውን አጋርተዋል። የኮሌራ በሽታ ‘ቪብሪዮ ኮሌሬ’ በተሰኘ የባክቴሪያ ዓይነት የሚመጣ አደገኛ ተላላፊ በሽታ ነው ይላሉ።

እንደ እሳቸው ሀሳብ የበሽታው ዋና ዋና ምልክቶች አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት ናቸው። በሽታው በተበከለ ምግብ እና ውኃ አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚተላለፍ አቶ አሞኜ ተናግረዋል። በአብዛኛው ሰዎች ንጽህናው ያልተጠበቀ ውኃ ሲጠጡ እና ምግብ ሲመገቡ በበሽታው በቀላሉ ይያዛሉ ነው ያሉት።

በንጽህና ያልተያዙ የመመገቢያ ቁሳቁስ እንዲኹም ያልበሰሉ አትክልቶችን እና ፍራፍሬዎችን መመገብ ለበሽታው መከሰት ምክንያቶች ይኾናሉ ብለዋል ። በስለው በሞቃት ቦታ ለረጅም ጊዜ የተቀመጡ ምግቦችም ኮሌራን ሊያስይዙ ይችላሉ በማለት አቶ አሞኘ ጥንቃቄን ይመክራሉ። መጸዳጃ ቤትን በአግባቡ ባለመጠቀም ኮሌራ ይከሰታል ያሉት አቶ አሞኜ ከኮሌራ ታማሚ ጋር የሚደረግ ጥንቃቄ የጎደለው ንክኪ ለበሽታው ይዳርጋል።

ኮሌራን እንዴት መከላከል ይቻላል? የበሽታው ዋነኛ መንሥኤ የጽዳት ጉድለት በመኾኑ የሚበሉ እና የሚጠጡ ነገሮችን እንዲኹም የአካባቢን ንጽህናን ሣይንሳዊ በኾነ መንገድ በመጠበቅ በሽታውን መከላከል እንደሚቻል አቶ አሞኜ አሳስበዋል።

ሁልጊዜ ውኃ አፍልቶ በማቀዝቀዝ ወይም በውኃ ማከሚያ ኬሚካል የታከመ ውኃ መጠቀም፣ ምግብን በሚገባ አብስሎ በትኩሱ መመገብ፣ የምግብ ዕቃዎችን በንጹህ ውኃ ወይም በኬሚካል በታከመ ውኃ ማጠብ እና መጠቀም፣ መጸዳጃ ቤትን አዘጋጅቶ በአግባቡ መጠቀም እና የኮሌራ በሽተኛን ሰገራ በአግባቡ በማስወገድ የኮሌራ በሽታን መከላከል እንደሚቻል ነው አቶ አሞኜ የመከሩት።

እጅን ከመጸዳጃ ቤት መልስ፣ ምግብ ከማዘጋጀት፣ ምግብ ከማቅረብ፣ ምግብ ከመመገብ በፊት፣ ሕጻናትን ካጸዳዱ በኋላ፣ ሕጻናትን ጡት ከማጥባት በፊት፣ በበሽታው ለተያዙ ሰዎች እንክብካቤ ካደረጉ በኋላ በሳሙና መታጠብ ግድ ይላል።

በበሽታው የሞቱ ሰዎችን አስክሬን የነካ ሰውም እጁን በሳሙና እና ሳሙና ከሌለ በአመድ በሚገባ መታጠብ እንደሚገባውም ቡድን መሪው አስገንዝበዋል።

ማንኛውንም ከቤት የሚወጣ ደረቅ ወይም ፈሳሽ ቆሻሻ አካባቢን እንዳይበክል በአግባቡ በተገቢ ሥፍራ ማስወገድ የኮሌራ መከላከያ ሌላኛው ዘዴ ነው።

በኮሌራ በሽታ የታመመን ሰው ልብስ በፈላ ውኃ መቀቀል ወይም በበረኪና፣ በልብስ ማጽጃ ሳሙና ዘፍዝፎ ማጠብ ግድ ይላል።

የበሽታው ምልክት የታየበትን ሰው በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም በመውሰድ የሕክምና ርዳታ እንዲያገኝ ማድረግም ሌላው የኮሌራ በሽታ ስርጭት መከላከያ መንገድ ነው፡፡

የኮሌራ በሽታ በቀላሉ የሚታከም የበሽታ ዓይነት ነው፤ ነገር ግን አፋጣኝ ሕክምና ካላገኘ ቶሎ ሰውን ለሞት ይዳርጋል ነው ያሉት ቡድን መሪው።

ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በራያ ቆቦ ወረዳ እና በቆቦ ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን ጎበኙ።
Next articleየአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ያሠለጠናቸው 33ኛ ዙር ምልምል የፓሊስ አባላት ጎንደር ከተማ ሲገቡ አቀባበል ተደረገላቸው።