ከዛሬ ጀምሮ ግለሰቦች በወር እስከ 1 ሚሊዮን፣ ኩባንያዎች ደግሞ እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ነው ከባንኮች ማውጣት የሚችሉት።

217

ከባንኮች የሚወጣን ጥሬ ገንዘብ የሚገድብ መመሪያ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ።

የብሄራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ዛሬ በሰጡት መግለጫ መመሪያው የገንዘብ ዝውውርን ወደ ስርአት በማስገባት ወንጀልንና የግብር ስወራን ለመከላከል በከፍተኛ ሁኔታ ያግዛል ብለዋል።

ዛሬ የሚተገበረው አዲሱ መመሪያ ለግለሰብ በቀን እስከ 200 ሺህ እና በወር ደግሞ እስከ 1 ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ ማውጣት ሲፈቅድ ለኩባንያዎች ደግሞ በቀን እስከ 300 ሺህ ብር እና በወር እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ድረስ በጥሬ ገንዘብ ማውጣት ይችላሉ ተብሏል።

ወጪ የጥሬ ገንዘብ ገደቡ መጠን ላይ ምንም ለውጥ ሳያሳድር ከተገደበው የጥሬ ገንዘብ በላይ ለሚፈልጉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ከአካውንት ወደ አካውንት ወይንም በቼክ ወይንም ደግሞ በሲፒኦ ተጨማሪ ክፍያን መፈጸም ይችላሉ ተብሏል።

መመሪያው በልዩ ሁኔታ መታየት ያለባቸው ከፍያዎችን በተመለከተም የራሱ ሂደት አለው። ኢዜአ እንደዘገበው የልዩ ሁኔታ ክፍያም ለየባንኮች ፕሬዚዳንቶች ስልጣን እንደሰጠና ውሳኔ አሳልፈው ክፍያው የተፈፀመ እንደሆነም በየሳምንቱ ለብሄራዊ ባንክ በሚያደርጉት ሪፖርትና ክትትል እንደሚያልፍም ተነግሯል።

መመሪያውን ጥሶ የተገኘ ባንክም ከፈጸመው ክፍያ የ25 በመቶ ጥብቅ ቅጣት እንደሚፈጸምበትም ተነግሯል።

መመሪያው በሁሉም ባንኮችና አነስተኛና ጥቃቅን የፋይናንስ ተቋማት ላይ ይተገበራል።

Previous articleበመጪው የመኸር ወቅት ተጨማሪ ምርት ለማግኘት ከ60 ሺህ ሄክታር መሬት ለአልሚዎች ሊተላለፍ ነው፡፡
Next articleበዋግ ኽምራና ላልይበላ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መቋረጡ ነዋሪዎችን ለምሬት ዳርጓል፡፡