
ባሕር ዳር: ሚያዚያ: 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት በፈጠራ እና ክህሎት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
የትምህርት፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴሮች ከአፍሪካ ብሬይንስ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት “ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025” ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባዔው የአፍሪካ ሀገራት የዘርፉ ሚኒስትሮች፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የትምህርት አጋር ድርጅቶች እና የግሉ ሴክተር ባለሃብቶች ተሳትፈዋል፡፡
ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ቀጣዩን ትውልድ ለመገንባት ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ እና ክህሎት ወሳኝ መኾናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ትምህርት እና ክህሎትን ማዕከል በማድረግ በትምህርት ቤት ግንባታ እና መሠረተ ልማት ማሻሻል፣ በዲጂታል ኔትዎርክ ግንባታ እንዲሁም በፈጠራ እና ክህሎት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው አሁን ያለንበት የዓለም ሁኔታ በጣም የተወሳሰበ በመኾኑ መጪውን ትውልድ እና ወጣት በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ እና በክህሎት ማዘጋጀት ይጠበቃል ብለዋል።
በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ እና በክህሎት ዘርፍ የሚደረገው ውይይትም በትክክል ለአፍሪካ ለውጥ መሠረት የሚጣልበት ሊኾን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ለሦስት ቀናት በሚካሄደው ጉባዔ ከትምህርት፣ አይሲቲ እና ክህሎት ጋር የተያያዙ ወሳኝ አጀንዳዎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
