
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የስጋ ደዌ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃም ለ26ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው። ቀኑ በባሕር ዳር ከተማም “የሥጋ ደዌ በሽታን አንዘንጋው” በሚል መሪ መልዕክት እየተከበረ ነው። ቀኑን የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የጤና ቢሮ እና የክልሉ ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ማኀበር በጋራ ነው እያከበሩት የሚገኙት።
የክልሉ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በስጋ ደዌ ተጠቂዎች ዙሪያ ያለውን የማኀበረሰቡ የተዛባ አመለካከት፣ የመረጃ እጥረት ማረም ያስፈልጋል ብለዋል። ውጤታማ ያልኾነውን አደረጃጀት በማስተካከል በማኀበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እኩል ተሳታፊ ብሎም ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባልም ነው ያሉት።
ቢሮው የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል ብለዋል። የተዛባውን አመለካከት ለመለወጥም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ነው ያሉት። የክልሉ ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ማኀበር ሊቀ መንበር አቶ ምንይችል ደምለው በየማዕዘኑ በጎስቋላ አኗኗር ውስጥ የሚገኙ የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ሕይዎት እንዲለወጥ የተጀመሩ መልካም ጅምሮች እንዲሰፉ እና በሽታው እንዳይዘነጋ በርብርብ መሥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በዕድሜ የገፉ እና በአካል ጉዳት ሳቢያ አልጋ ላይ የቀሩ ተጠቂዎችን መንከባከብ ብሎም መደገፍ ይገባል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!