
ጎንደር :ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምርት ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ እየሠራ መኾኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። የጎንደር ንጋት ከፍተኛ ሰብል አምራቾች ግብይት እና ግብዓት ኅብረት ሥራ ማኅበር በ56 አምራች ገበሬዎች የተቋቋመ ሲኾን በግብርና ምርቶች ላይ እሴትን በመጨመር ለገበያ እያቀረበ ይገኛል።
ማኅበሩ ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ካፒታል ወደ ሥራ የገባ ሲኾን በሰሊጥ፣ በጥጥ፣ በማሾ እና አኩሪ አተር ምርቶች ላይ እሴትን በመጨመር ለገበያ ያቀርባል። ማኅበሩ በ2017 የምርት ዘመን ከ20 ሺህ ኩንታል በላይ የጥጥ ምርት ለመሠብሠብ አቅዶ ከ6 ሺህ ኩንታል በላይ በመሠብሠብ እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ እየሠራ መኾኑን የማኅበሩ ከፍተኛ ቦርድ ሠብሣቢ ወርቅነህ ማሩ ተናግረዋል።
ምርቶች ላይ እሴትን በመጨመር ለኮምቦልቻ ከተማ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች፣ ለዓባይ ጋርመንት እና ለባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ምርቶችን እያቀረቡ መኾኑንም ገልጸዋል። ማኅበሩ በኪራይ ቦታ እና ማሽን እየሠራ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ወርቅነህ መንግሥት የቦታ እና የብድር አገልግሎት እንዲያሟላ ጠይቀዋል።
በምርቶች ላይ እሴትን በመጨመር ከ3 ሺህ በላይ የጥጥ ቦንዳ እና ወደ 3 ሺህ የሚጠጋ የጥጥ ፍሬ ምርትን ለገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑን የማኅበሩ ሥራ አሥኪያጅ ሊዲያ ዳምጤ ተናግረዋል። ማኅበሩ በግብርና ምርቶች ላይ እሴትን ጨምሮ ለገበያ ማቅረቡ ግብርናን ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሳደግ ያለው ሚና ጉልህ መኾኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋሁን ተሰማ ተናግረዋል።
በዞኑ 460 መሠረታዊ ማኅበራት እና አራት ዩኒየኖች መኖራቸውን በማንሳት በሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበር፣ በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር እና በገንዘብ ቁጠባ ብሎም ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዘርፍ መሠማራታቸውን ገልጸዋል።
ማኅበራቱ ከ900 በላይ ለሚኾኑ ግለሰቦች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል። ማኅበሩ ያጋጠመውን የቦታ እና የብድር ችግር ለመቅረፍ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
በማኅበሩ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው አካላት በበኩላቸው በሥራው ተጠቃሚ መኾናቸውን አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን