
ባሕር ዳር : ሚያዝያ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 5ኛውን የምሥራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት አባል ሀገራት የስፖርት ውድድር አስጀምረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የአፍሪካውያን ሰላም፣ ዕድገት እና ብልጽግና ያለ ፖሊስ ተቋማት ጥንካሬ እና ብቃት የሚታሰብ አይደለም ነው ያሉት።
ዛሬ የኢትዮጵያ ፖሊስ የተመሰረተበትን 116ኛ ዓመት በዓልን በማስመልከት የሚካሄደውን 5ኛውን የምሥራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት አባል ሀገራት የስፖርት ውድድር በውቧ አዲስ አበባ በይፋ አስጀምረናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዘመናዊ የፖሊስ ተቋምን ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት በመመስረት ግንባር ቀደምና ተምሳሌት ሀገር ናት።
ባለፉት ሰባት ዓመታት ያደረግነው የጸጥታ ተቋማት ሪፎርም ደግሞ ፖሊስን ይበልጥ ዘመናዊ፣ ይበልጥ ዝግጁ፣ ይበልጥ ደረጃውን የጠበቀ፣ ይበልጥ ግዳጅ ፈጻሚ እያደረገው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ኢትዮጵያንና አፍሪካን በዓለም መድረክ ያስጠሩ ስመ ጥር ስፖርተኞችን ያፈራ ተቋም ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አፍሪካዊ የሆኑ ስፖርታዊ ኩነቶችን እንዲያዘጋጅ ታሪኩም ልምዱም ይረዳዋል፡፡ አፍሪካውያን አፍሪካን በሚመጥን ደረጃ ተባብረን መሥራት አለብን ብለዋል።
በየአካባቢያችን ያለንን ዕውቀት፣ ልምድ፣ ቴክኖሎጂና ብቃት ደምረን ከተጠቀምን የተሻለ የፖሊስ ተቋም የመገንባት ሕልማችንን እውን ማድረግ እንችላለን፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅትም ይሄንን ፖሊሳዊ ኅብረትና ወዳጅነት ያጠናክራል። ለአንድ ዓላማ ተቀራርቦ የመሥራት ባሕልን ያዳብራል። ይህ የስፖርት ፌስቲቫል ኅብረታችን የበለጠ የሚጠናከርበት እንደሚሆን አምናለሁ ነው ያሉት።
መልካም የውውድር ጊዜ እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን