“ደንብ አሥከባሪዎች የማኅበረሰቡን የጸጥታ ችግር እየቀረፉ ነው”

40

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ አንጓች እንየው በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የተንታ ጭርቆስ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ በጥምር ግብርና ዘርፍ ተሰማርተው በግ እና ሰንጋ አስረው በማድለብ ለገበያ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ በትንሳዔ በዓል ዋዜማ በርካታ በጎችን ለገበያ አውጥተው እንደሸጡ የተናገሩት ወይዘሮ አንጓች ግለሰቦች ያልገዟቸውን በጎች እንደገዟቸው አድርገው እና አዋክበው ለመወሰድ ሲሞክሩ ደንብ አስከባሪዎች ፈጥነው እንደደረሱላቸው ተናግረዋል፡፡

ሌቦች ንብረቴን በጠራራ ፀሐይ ሊዘርፉኝ ሲሞክሩ ደንብ አስከባሪዎች ታድገውኛልና ሊመሰገኑ ይገባቸዋል” ነው ያሉት፡፡ ሌላው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ አቶ ጌጡ አድማሱ በመኖሪያ ቤታቸው በቅርብ ርቀት የዶሮ እና እንቁላል መሸጫ በመኖሩ አካባቢው ለመጥፎ ሽታ ተዳርጎ ቆይቷል ይላሉ።

በቅርቡ ግን የባሕር ዳር ደንብ አሥከባሪዎች ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ በአካባቢው ቆሻሻ እንዳይጣል እና በየቦታው እርድ እንዳይከናወን ማድረጋቸው ከችግሩ እንደታደጓቸው ተናግረዋል፡፡ አካባቢውም ጽዱ እንዲኾን የደንብ አስከባሪዎች ሚና ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ደንብ ማስከበር መምሪያ ኀላፊ ኃይለ ሚካኤል አርዓያ የደንብ አስከባሪዎች የደንብ ልብስ ስላልነበራቸው ከሌላው ሰው ለመለየት አስቸጋሪ ኾኖ መቆየቱን አውስተዋል፡፡

በቅርቡ ግን ከተማ አሥተዳደሩ ደንብ አስከባሪዎችን አረንጓዴ የደንብ ልብስ በማልበሱ ኅብረተሰቡ በቀላሉ መረጃ እና ጥቆማ እንድሰጣቸው አድርጓል ነው ያሉት፡፡ ከመከላከያ ሠራዊት፣ አድማ ብተና፣ ፖሊስ እና ሚሊሻ ጋር በቅንጅት ተናበው እንዲሠሩ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ በርካታ ገበያዎች ቢኖሩም ከመጨናነቃቸው የተነሳ ዋና ዋና ጎዳናዎች ሳይቀሩ ይዘጉ ነበር ያሉት መምሪያ ኀላፊው ደንብ አስከባሪው ኃይል በአግባቡ በመሥራቱ የኅብረተሰቡን ዘርፈ ብዙ የደህንነት ሥጋት መቀነስ ችሏል ነው ያሉት፡፡ በባሕር ዳር ከተማ ከፍተኛ ሌባ እና ሀሰተኛ ገንዘብ አዘዋዋሪ ነበሩ ያሉት መምሪያ ኀላፊው ደንብ አስከባሪው ኃይል ከኅብረተሰቡ ጋር በመኾን መንጥሮ በማወጣት ለሕግ ማቅረባቸውንም ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን በንቃት ከጠበቁ፣ ካጸዱ እና ካለሙ ባሕር ዳር በሁሉም ዘርፍ ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኝዎቿ ምቹ ትኾናለች ነው ያሉት። የአማራ ክልል ትልልቅ ከተሞች የባሕር ዳርን የደንብ ማስከበር ተሞክሮ ወስደው መተግበር ጀምረዋል ብለዋል፡፡ ሐረር እና ሐዋሳ ከተሞችም ከባሕር ዳር ከተማ ልምድ ለመቅሰም መጠየቃቸውን መምሪያ ኀላፊው አንስተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበኢትዮ ቴሌኮም የአክሲዮን ሽያጭ ላይ ከ47ሺህ በላይ ባለሀብቶች ተሳትፈዋል።
Next article” አፍሪካውያን አፍሪካን በሚመጥን ደረጃ ተባብረን መሥራት አለብን” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ