በኢትዮ ቴሌኮም የአክሲዮን ሽያጭ ላይ ከ47ሺህ በላይ ባለሀብቶች ተሳትፈዋል።

35

አዲስ አበባ: ሚያዝያ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም ባለፈው ጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም የ10 በመቶ የአክሲዮን ሽያጭ በይፋ ማስጀመሩ ይታወሳል። የ10 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ሽያጩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በይፋ ያስጀመሩት ሲኾን ደንበኞች ሸሩን በቴሌ ብር መተግበሪያ ሲገዙ መቆየታቸውን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬሕወት ታምሩ ገልጸዋል።

ዋና ሥራ አሥፈጻሚዋ የኩባንያውን የ10 በመቶ የአክሲዮን ሽያጭ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኅን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የአክሲዮን ሽያጩ በሁለት ምዕራፍ የተካሄደ ሲኾን የመጀመሪያው ምዕራፍ ከጥቅምት 07/2017 ዓ.ም እሰከ ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ ከታኅሣሥ 25/2017 እሰከ የካቲት 07/2017 ዓ.ም ሲካሄድ መቆየቱን አንስተዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም የሃብት መጠን 100 ቢሊዮን ብር መኾኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አሥፈጻሚዋ ከዚህ ውስጥ ለሽያጭ የቀረበው 10 በመቶ ነው ብለዋል። ለሽያጭ የቀረበው የአንድ አክሲዮን ዋጋ 300 ብር መኾኑንም አስገንዝበዋል። ዝቅተኛ መግዛት የሚቻለው ሼር 33 መኾኑን እና በብር ሲተመን 9 ሺህ 900 ብር እንደኾነም ዋና ሥራ አሥፈጻሚዋ ገልጸዋል።

አክሲዮኑ መሸጥ ከተጀመረ ጀምሮ 47 ሺህ 377 ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች መሳተፋቸውን ነው የኩባንያው ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ያስታወቁት። እነዚህ ተሳታፊዎችም 10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሸር መግዛታቸውን ጠቁመው በዚህም ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ ብር ግዥ መፈጸም ተችሏል ነው ያሉት።

በመጀመሪያው ዙር 43 ሺህ 848 ዜጎች የተሳተፉ ሲኾን 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን አክሲዮኖች መግዛት ችለዋል። በዚህም 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ግዥ መፈጸም ተችሏል ብለዋል። በሁለተኛው ዙር ደግሞ 3 ሺህ 529 ባለሀብቶች የተሳተፉ ሲኾን በዚህም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሸር በ571 ሚሊዮን ብር መሸጥ ተችሏል ብለዋል።

በአጠቃላይ በ121 ቀናት ውስጥ ለመሸጥ ከታቀደው 100 ሚሊዮን አክሲዮን 10 ነጥብ 7 ሚሊዮን አክሲዮን መሸጡን ዋና ሥራ አሥፈጻሚዋ አረጋግጠዋል። በቀጣይ ያልተሸጡ ሸሮችን ለመሸጥ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ባስቀመጠው ሕግ እና ደንብ መሠረት ለኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለመሸጥ በዝግጅት ላይ መኾኑ ተመላክቷል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየደሴ ከተማ አሥተዳደር በዝቅተኛ እና መካከለኛ ኑሮ ለሚገኙ ኑዋሪዎች የጋራ መኖሪያ ቤት ሊገነባ ነው።
Next article“ደንብ አሥከባሪዎች የማኅበረሰቡን የጸጥታ ችግር እየቀረፉ ነው”