የደሴ ከተማ አሥተዳደር በዝቅተኛ እና መካከለኛ ኑሮ ለሚገኙ ኑዋሪዎች የጋራ መኖሪያ ቤት ሊገነባ ነው።

101

ደሴ: ሚያዝያ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማዋ ነዋሪዎች የረጅም ጊዜ ጥያቄ የኾነውን እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለመመለስ ጊዜ ተወስዶ ሲሠራ መቆየቱን የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ተናግረዋል። በከተማው ከሚኖረው ሕዝብ 57 በመቶ ያህሉ የራሱ መኖሪያ ቤት የሌለው መኾኑ የችግሩን አሳሳቢነት እንደሚያሳይም ነው ከንቲባው የገለጹት።

በዚህ ዓመት በዝቅተኛ እና መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች ቅድሚያ ተሰጥቶ ይሠራል ያሉት አቶ ሳሙኤል ይህ ግን ሌሎች የከተማ ነዋሪዎችን አያካትትም ማለት እንዳልኾነም አብራርተዋል። ደሴ ከተማ በተራራ የተከበበች እና የመሬት እጥረት ያለባት በመኾኗ ይህን ችግር ታሳቢ ያደረገ የመፍትሔ እርምጃ መወሰዱንም ነው አቶ ሳሙኤል የገለጹት። በዚህ መሰረት የጋራ መኖሪያ ሕንጻ መገንባት አማራጭ ኾኖ መቅረቡን ነው ያነሱት።

የጋራ መኖሪያ ሕንጻ ደሴ ከተማ ከአለባት የመሬት ጥበት እና ከወጭ ቆጣቢነቱ አንጻር ተመራጭ መኾኑንም ነው አቶ ሳሙኤል የተናገሩት። ከሚያዝያ 20 ቀን ጀምሮ የመጀመሪያው ዙር የማደራጀት ሥራ ይሠራል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው “በመጀመሪያ ዙር 28 ሺህ ዜጎችን የጋራ መኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ እየተሠራ ነው” ብለዋል።

በሁለተኛው ዙር ደግሞ 22 ሺህ ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም የደሴ ከተማ አሥተዳደር አስታውቋል። ደሴ ከተማን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ሳሙኤል የሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ሕንጻዎች የተለያየ ደረጃ ቢኖራቸውም ከፍታቸው ግን ባለ አምስት ወለል ኾኖ ከባለ አንድ መኝታ እስከ ባለ ሶስት መኝታ ያላቸው ተመሳሳይ ሕንጻዎች ይኾናሉ ነው ያሉት።

የሕንጻዎቹ ከፍታ ተመሳሳይ መኾን የከተማዋን ውበት ለመጠበቅ ያለመ መኾኑንም አንስተዋል። ቤት ፈላጊ የከተማዋ ነዋሪዎች ፍላጎታቸውን እና አቅማቸውን መሰረት በማድረግ ማለትም በባለ አንድ መኝታ፣ በባለ ሁለት መኝታ እና በባለ ሦስት መኝታ ቤቶች መደራጀት አለባቸው ብለዋል።
አንድ ሰው በአንድ ማኅበር በተመሳሳይ ፍላጎት ብቻ መደራጀት እንዳለበትም ገልጸዋል።

ባለ አንድ መኝታ ቤት ፈላጊ ወገኖች ባለ አንድ ከሚፈልጉ 72 ሰዎች ጋር መደራጀት ግድ መኾኑንም አንስተዋል። ባለ ሁለት መኝታ ፈላጊዎች ደግሞ 54 ሰዎች በአንድ መደራጀት አለባቸው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ባለ ሦስት መኝታ ፈላጊዎች 42 ኾነው ሊደራጁ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የመንግሥት ሠራተኞች መደራጀት የሚችሉት በሚሠሩበት ተቋም ብቻ መኾኑን የተናገሩት አቶ ሳሙኤል ሌሎች የከተማ ነዋሪዎች ደግሞ በክፍለ ከተማ እና በቀበሌ መዋቅሩ በኩል አስፈላጊው ማጣራት ከተሠራ በኋላ አደረጃጀቱን ይቀላቀላሉ ብለዋል። በተቋማት የሚደራጁ ቤት ፈላጊዎች ከዚህ ቀደም ሲሠሩበት ከነበረው አካባቢ ቦታ አለማግኘታቸውን የሚገልጽ መረጃ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል አቶ ሳሙኤል።

ከተማ አሥተዳደሩ አስፈላጊውን ሁሉ ማጣራት እንደሚያደርግም ገልጸዋል። አሠራሩን ለማዘመንም ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ዝግጅት ተጠናቋል ተብሏል። የከተማዋን ነዋሪዎች የቤት ፍላጎት ለማሟላት 213 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን እና ከዚህ ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚኾነው የካሳ ክፍያ እና ተያያዥ ተግባራት መጠናቀቃቸውን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።

ነዋሪዎች ከሚሠሩባቸው ተቋማት እና ከክፍለ ከተማ ውጭ እናደራጃለን በሚሉ ደላሎች እና ሕገ ወጦች እንዳይታለሉ ያሳሰቡት ከንቲባው መደራጀት የሚቻለው መንግሥት በዘረጋው መዋቅር ብቻ መኾኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል። ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚሠራው ሥራ ውስጥ የራሳቸውን ጥቅም ለማግበስበስ የሚሯሯጡ አካላት መፈጠር፣ ወቅታዊ የጸጥታ ችግር እና ጉዳይ እናስፈጽማለን በማለት ውዥንብር የሚፈጥሩ ደላሎች መበራከት በስጋት የሚጠቀሱ ናቸው ያሉት ከንቲባው እነዚህን ችግሮች ለማስቀረት ሕዝቡ ከጎናቸው እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርበዋል።

የከተማ መሪው፣ የጸጥታ ኀይሉ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለሥራው ስኬታማነት ቀን ከሌሊት እንደሚሠሩ እና እየሠሩ መኾኑንም አንስተዋል። ከሚያዚያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ባለ አንድ መኝታ ቤት ፈላጊ 125 ማኅበራት፣ ባለ ሁለት መኝታ ቤት ፈላጊ 275 ማኅበራት እና ባለ ሦስት መኝታ ቤት ፈላጊዎች 100 ማኅበራት ይደራጃሉ ነው የተባለው።

በመጀመሪው ዙር የተደራጁት ቤት ፈላጊዎች ቦታ ከተረከቡ በኋላ በሁለተኛው ዙር ደግሞ 22 ሺህ ወገኖች ተደራጅተው የቤት ባለቤት እንዲኾኑ እየተሠራ ነውም ብለዋል።

ዘጋቢ:- አሊ ይመር

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“በክልሉ የተሟላ ሰላም ለማምጣት እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤት እያመጣ ነው” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)
Next articleበኢትዮ ቴሌኮም የአክሲዮን ሽያጭ ላይ ከ47ሺህ በላይ ባለሀብቶች ተሳትፈዋል።