“በሙስና የተገኘ ገንዘብን የመሰወር እና ሽብርተኝነትን ለመደገፍ የሚደረጉ ጥረቶችን መከላከል ይገባል” የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ

37

አዲስ አበባ:ሚያዝያ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንቦችን እና መመሪያዎችን አክብሮ የመሥራት ቀንን ለ4ኛ ጊዜ አክብሯል። በዓሉ የተከበረው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት የመንግሥት መስሪያ ቤት ኀላፊዎች የባንኮች ተወካዮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ነው ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በየጊዜው አይነቱ እና ባሕሪውን እየለዋወጠ ለሚገኘው የወንጀል ድርጊት ተገቢ እና ተመጣጣኝ ዝግጁነት እና ምላሽ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በባንኮች የሚንቀሳቀሱ ገንዘቦችን ሕጋዊነት በሚገባ በመቆጣጠር ታክስ የማሸሽ፣ በሙስና የተገኘ ገንዘብን የመሰወር እና ሽብርተኝነትን ለመደገፍ የሚደረጉ ጥረቶችን መከላከል ይገባል ብለዋል።

ለዚህም የደንበኞችን ማንነት በሚገባ ማወቅ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ መኾኑንም ጠቁመዋል። ባንኮች እና ሌሎች የገንዘብ ተቋማት እርስ በእርስ በመተባበር የፋይናንስ ሴክተሩን ደኅንነት ለማስጠበቅ በጋራ መሥራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሪስክ አሥተዳደር እና ኮምፕሊያንስ ምክትል ፕሬዝዳንት ፍሬው ገብረሥላሴ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንቦችን እና መመሪያዎችን አክብሮ የመሥራት (የኮምፕሊያንስ) ባሕልን ለመገንባት እና ለማስረጽ ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ሁሉም ባለድርሻ አካላት የፋይናንስ ሥርዓቱን ጤንነት ለማስጠበቅ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ እና የባንኩ የሥራ ኀላፊዎች ደንቦችን እና መመሪያዎችን አክብሮ የመሥራት (የኮምፕሊያስ) ባሕል በባንኩ እንዲዳብር የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክርው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል ፡፡

በመርሐ ግብሩ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች ባቀረቧቸው መነሻ ጹሑፎች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

ዘጋቢ፦ ራሔል ደምሰው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“በማንኛውም ወቅት መምህራን ላይ የሚደርስ ጥቃትን አጥብቀን እንቃወማለን” ዮሐንስ በንቲ (ዶ.ር)
Next article“በክልሉ የተሟላ ሰላም ለማምጣት እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤት እያመጣ ነው” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)