
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከ60 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ለአዲስ አልሚዎች ለማስተላለፍ ዝግጅት ላይ መሆኑን የክልሉ ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ አስታወቀ።
የተለያየ አፈጻጸም ችግር ያለባቸውን በመንጠቅ አዲስ ለሚያለሙ ባለሀብቶች ለማስተላለፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ኃላፊ ግዛት አብዩ ተናግረዋል።
በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ምርታማነቸውን እንዲጨምሩ ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል።
መሬት በጨረታ፣ በጊዜያዊነት፣ በመደበኛ የሊዝና በጨረታ በጊዜያዊነት መርቶ በማቅረብ በኩልም እየተሠራ ስለመሆኑ ኃላፊው አመልክተዋል። በመጪው የመኸር ወቅት በምዕራብ ጎጃም፣ አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር በሰፊው ለማልማት ታስቧል።
የእርሻ ወቅት ከመድረሱና ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ምርትና ምርታማነት እንዳይቀንስ ማምረት የሚችል የገጠር ኢንቨስትመንት መሬት ጾም እንዳያድርና የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ከ60 ሺህ ሄክታር በላይ የኢንቨስትመንት መሬት በውድድር ማስተላለፍ እንዳስፈለገ ነው የክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ የገለጸው።
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡