
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ የክልሉ መንግሥት በርብርብ ከሚሠራቸው ተግባሮች መካከል የጤና መድኅን አገልግሎት አንዱ ነው ብለዋል፡፡
የጤና መድኅን አገልግሎት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች ከፍተኛ ጠቀሜታ እየሰጠ መኾኑን ገልጸዋል። አንድ ሰው በዓመት አንድ ጊዜ በከፈለው መዋጮ ቤተሰቡ ሲታመም ዓመቱን ሙሉ ያለምንም መጨናነቅ የአባልነት መታወቂያ ደብተር ብቻ በመያዝ የጤና አገልግሎቱን ማግኘት ያስችለዋል ብለዋል።
እንደ ክልል በማኅበረሰብ ጤና መድኅን አገልግሎት ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት ሲስተር ክሽን በ2017 ዓ.ም ከ4 ሚሊዮን በላይ ማኅበረሰብ የጤና መድኅን አባል ለማድረግ እየተሠራ ነው መኾኑን ገልጸዋል።
ለተግባራዊነቱ ከቀበሌ እስከ ክልል ያሉ መሪዎች ትኩረት ሰጥተው በመሥራታቸው 80 ነጥብ 1 በመቶ የሚኾኑ የክልሉን አባውራዎች እና እማውራዎች የጤና መድኅን አባል ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
አገልግሎቱን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት 670 ሚሊዮን ብር መድቦ እየተንቀሳቀሰ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
”ጤና ከሌለ ምንም ነገር አይኖርም” ያሉት ሲስተር ክሽን ባለሀብቶች ፣ ነጋዴዎች እና ሌሎችም የማኅበረሰብ ክፍሎች አስተዋጽኦ ቢያደርጉ ከፍለው መታከም የማይችሉ ወገኖችን ጤና በቀላሉ መጠበቅ ይቻላል ነው ያሉት።
የጤና መድኅን የመጠቀሚያ ደብተር በየዓመቱ እንደሚታደስም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን