“ዜጎችን በተሻለ የሕይዎት ደረጃ እና ጤንነት እንዲኖሩ ከማድረግ የበለጠ ምንስ ሰብዓዊነት አለ” ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)

42

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የካዛንቺስ የኮሪደር ልማት እስካሁን በከተማዋ ከተገነቡት የኮሪደር ልማት ሥራዎች በውስጡ ባስተሳሰራቸው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች የተለየ ገጽታን የፈጠረ መኾኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) ገልጸዋል።

የቀደመውን የአካባቢውን ምስቅልቅል ሁኔታ በዐይነ ህሊናው ለሚያይ፣ በተለይ በዕለት ተዕለት ሕይዎቱ አካባቢውን ሲያስተውል ለነበረ የከተማው ነዋሪ በኮሪደር ልማቱ የተፈጠረው አዲስ እና ውብ ገጽታ በምናብ ከሚያውቀው የውብ እይታ እና ሀሴት ነጸብራቅ ተምሳሌት ከኾነው የገነት ፀዳል አንዳች ሃሳብ ተውሶ ከተማችንን ወደ ምድራዊ ገነት እየቀየርናት ይኾን? ብሎ እንዲጠይቅ ያነሳሳል ብለዋል።

“ይህን የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ የቀየረ የካዛንችስን ድንቅ ሥራ አለማድነቅ ንፉግነት ነው” ብለዋል። ከሰሞኑም የከተማችን ሰው ተኮርና ሁለንተናዊ ሀገራዊ ለውጥ አካል የኾነው የካዛንቺስ ኮሪደር ልማት፣ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በይፋ ተመርቆ ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት ኾኗል ነው ያሉት ሚኒስትሩ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው።

የካዛንቺስ የኮሪደር ልማት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት አካል ነው ብለዋል። የኮሪደር ልማቱ ካዛንቺስን ውብ በማድረግ አካባቢውን ካላበሰው አዲስ ገጽታ ባሻገር በዘመናዊነቱም ይጠቀሳል ነው ያሉት። ለአዕምሮ ሀሴትን የሚፈጥሩ እና ለእይታ የሚማርኩ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር እና ጽዱ አካባቢን ለነዋሪው በመለገስ ሌላ አዲስ ተጫማሪ የመዝናኛ ስፍራን ለከተማዋ፣ በተለይም ለነዋሪዎቿ አበርክቷል ብለዋል፡፡

የከተማዋንም ገጽታ አንድ ደረጃ ክፍ ያደረገው ይህ ግንባታ የኢትዮጵያ ብልጽግና እና ትንሣኤ አይቀሬ መኾኑንም ያመላክተ ነው፡፡ ሁሉን ያቀናጀ የከተማ ግንባታ አካል በመኾኑ ለዘመናዊ ከተማ ግንባታችን ሞዴል ተደርጎ የሚወሰድም ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር እየተገነቡ ያሉ ኮሪደሮች ትስስር እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር የከተማዋ ገጽታ በመሠረታዊነት እየተቀየረ መኾኑን አይተናል፡፡ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እና “አዲስ አበባ” እያደረጓት ነው ብለዋል፡፡

ዘመናዊ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች መስፋፋታቸው እና የተሳለጡ መኾናቸው ለኮሪደር ልማት ሥራዎች እንደ ጀርባ አጥንት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ግንባታዎች የሰው እና የተሽከርካሪ መጓጓዣ መንገዶችን፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፤ የመብራት፣ የስልክ እና ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች፣ የመዝናኛና የማረፊያ ቦታዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሰፍራዎች ወዘተ የሚያካትቱ ናቸው ነው ያሉት፡፡

የመሠረተ ልማት ሥራዎቹ በከተሞች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማስተሳሰር በሁሉም አቅጣጫ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው፡፡ በመሠረተ ልማቶቹ ዝርጋታም ኾነ በመልሶ መልማት ከቦታው የሚነሱ ነዋሪዎች የሚዛወሩባቸውን የመኖሪያ መንደሮች ጭምር የሚያካትቱ ናቸው፡፡

መኖሪያ መንደሮቹ ዘመናዊ ከመኾናቸው ባሻገር ለነዋሪዎች እንዲመቹ እንደ ትምህርት ቤት፣ ወፍጮ ቤቶች፣ የዳቦ እና እንጀራ መጋገሪያ እንዲሁም የአቅመ ደካሞች መመገበያ ማዕከሎችን ያካተቱ ናቸው፡፡ ልማቱ ሁሉን አቀፍ፣ አካታች እና ሰው ተኮር ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው።

የመዝናኛ ስፍራዎቹ ከማዝናናት ባሸገር አዕምሮን ለማሳረፍ፣ ከራስ ጋር ለመታረቅ፣ በንባብ አዕምሮን ለመገንባት፣ በስፖርት አካልን ለማበልፀግ ታሳቢ ተደርገው የተገነቡ ናቸው። የአረንጓዴ ስፍራዎች ከአካባቢያቸው ጋር የተስማሙ ዘላቂ የከተማ ልማት የመገንባት አቅጣጫን የተከተሉ ናቸው።

ይህን ዘመናዊ፣ ሁሉን አካታች፣ ቅርስን በማቆየት ለዛሬው የተመቸ፣ ለነገው ትውልድ ተሻጋሪ የኾነን አኩሪ ሥራ አንዳንድ ሰዎች ባለማወቅም ይሁን ኾን ብለው “ብልጭልጭ ነገር” ብለው ሊያሳንሱት ሲሞክሩ ይታያል። አንዳንዶቹ ደግሞ ሰብዓዊነት ለምን አይቀድምም ሲሉ ይደመጣል። መነሻቸው ምንም ይሁን ምን ትችቶቹ ከሰው ተኮር ልማቱ እና ሀገርን በማበልፀግ ሕዝብ የተሻለ ሕይዎት እንዲኖር ለማድረግ ከተያዘው መሠረታዊ መርኾዎች ያፈነገጡ ናቸው ብለዋል።

ምክንያቱም የአንድ ከተማ ዕድገት ቁልፍ መለኪያ የሚባሉት ከላይ በዝርዝር የቀረቡ መሠረተ ልማቶች ምን ያክል አካታች በኾነ መንገድ ተሟልተዋል? ለነዋሪዎች ምቹ የኾነ አግልግሎት ቀርቧል ወይ? የሚለው ነው። ትችቱ፣ ከቁልፍ መሠረተ ልማቶቹ አንዱ በኾነው የመንገድ ዳር መብራት ጉዳይ የሚቀርብ ከሆነም እሱም ስህተት ነው።

ምክንያቱም በጣም አድጓል ተብለው ለከተሞች ደረጃ ለመፈረጅ ጥቅም ላይ ከሚውሉ መሥፈርቶች አንዱ በሌሊት ከተሞቹ ከሳተላይት በሚወሰዱ መረጃዎች ምን ያህል ብርሃናማ ናቸው የሚል ነው። ብርሃን በእጅጉ ደምቆ የሚታይበት ከተማ ብቁ መሠረተ ልማት ያሟላና ያደገ ተደርጎ ይወሰዳል። ነዋሪዎቹም ደስተኞች ሆነው የሚኖሩበት፣ ወንጀል በስፋት የማይታይበት እና የብልጽግና ተምሳሌት ተደርገው ይወሰዳሉ።

በአንጻሩ በጭለማ የተዋጡ ከተሞች መሠረተ ልማት ያልተገነቡላቸው፣ ወንጀል የሚበዛባቸው፣ ነዋሪዎቹም በምቾት እና በደህንነት ከመኖር አንፃር ተስፋ የሚያጡባቸው ናቸው። መጀመሪያ ሰብዓዊነት አይቀድምም ወይ ለሚሉት ደግሞ ምላሹ ከዚህ የተሻለ ምን ዓይነት ሰብዓዊነት አለ የሚል ነው፡፡ እጅግ ለመኖር አስቸጋሪ ከኾነና ከተጎሳቆለ አካባቢ፣ ንጹህ መጠጥ ውኃ እና የመጸዳጃ ስፍራ ከማይገኝበት፣ ሰው እና ተሽከርካሪ እየተጋፉ ከሚጓዙበት ውስብስብ እና ጭንቅንቅ መንገዶች እና አከባቢዎች በመውጣት እነዚህ ጉዳዮች በተሟሉበት ከባቢና አውድ መኖር እንዴት ሰብዓዊነትን ማጣት ይሆናል?

አዛውንቶች መውጫ እና መግቢያ አጥተው ከሚንከራተቱበት፣ በደሳሳ ጎጆ እንዲታፈኑ ከተገደዱበት፣ ህፃናት እና ወጣቶች ለማኅበራዊ ጠንቆች ከሚጋለጡባቸው አካባቢዎች ተነጥለው ለመኖር እጅግ ምቹ ወደ ኾኑ የተቀናጀ ማኅበራዊ አገልግሎት የሚያገኙባቸው፣ የተሻሻለ የኑሮ ዘይቤ ወዳሉባቸው አካባቢዎች መዛወራቸው እንዴት ሰብዓዊነትን መፃረር ተደርጎ ይወሰዳል? ይህ የሰብዓዊነት መለኪያውስ ምን ይሆን ያስብላል።

“ዜጎችን በተሻለ የሕይዎት ደረጃ እና ጤንነት እንዲኖሩ ከማድረግ የበለጠ ምንስ ሰብዓዊነት አለ?” ብሎ ህሊናን መጠየቅ ግድ ይላል፡፡ ለነገሩ ከተቺዎቹ በላይ ሕዝቡ፣ በተለይም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከካዛንቺስ ኮሪደር ልማት አስቀድመው የካዛንቺስ ልማት ተነሺዎች አዲስ ሕይዎት በጀመሩበት የገላን ጉራ አካባቢ ነዋሪዎቹን ባገኙበት ወቅት ነዋሪዎቹ ያሳዩት የማይረሳ የደስታና ሀሴት ብስራት ገላጭ መልዕክት እውነታውን አሳውቆናል።

በተለይ ምክንያት አልባ በሆነ የሁልጊዜ ጨለማ እይታ የሚተቹ ወገኖች መገንዘብ ያለባቸው ጉዳይ የከተማ ነዋሪዎችም እንደ የትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች ብቁ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን የማግኘት እና ምቹ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት ያላቸው መሆኑን ነው።

ለራስ የፖለቲካ ጥቅም ሲባል ሌላውን ደፍቆና አሳንሶ እንዲኖር ማድረግ ህሊና ቢስነት ነው። ዜጎች በራሳቸው እንጡራ ሃብት እና ከራሳቸው በሚሰበሰብ ግብር አካባቢያቸውን የማልማት መብት እንዳለቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡

በጥቅሉ ከአዲስ አበባ የምንወስደው ተሞክሮ የኮሪደር ልማት ስራ በስፋት የሚታይባቸው አካባቢዎች ዜጎች ተቺዎችን ወዲያ ብለው ከአስተዳደራቸውና ከጸጥታ ኃይል ጋር ተቀናጅተው እንዲሁም እጅ እና ጓንት ሆነው ሰላማቸውን በማስከበር መልማት ይኖርባቸዋል፡፡

መለስተኛ ችግር በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ያሉ ወገኖቻችንም እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞቻችንን ፈልግ የመከተል እና የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት መጠበቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህንን ሲያደርጉም ልማታቸው እየተፈጠነ፣ ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠ ይሄዳል፡፡ ካዛንቺስን አለማድነቅ ግን ንፉግነት ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና በሰኔ ወር እንደሚሰጥ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
Next articleከ80 በመቶ በላይ የሚኾኑ አባውራዎች እና እማውራዎችን የጤና መድኅን አባል ማድረጉን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።