በዚህ ወር የሙከራ ምርት ሊጀምር የነበረው ስኳር ፋብሪካ በስምንት ወራት ሊዘገይ ነው፡፡

187

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) የጣና በለስ የተቀናጀ የስኳር ልማት ፕሮጀክት በዚህ ወር የሙከራ ምርት ለመጀመር የነበረው እቅድ አለመሳካቱን አስታወቀ፡፡

በያዝነው ግንቦት ስኳር ለማምረት ዝግጅት እያደረገ የነበረው የጣና በለስ የተቀናጀ የስኳር ልማት ፕሮጀክት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት “እቅዴን ማሳካት አልቻልኩም” ብሏል፡፡

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጃዊ ወረዳ የሚገኘው ጣና በለስ የተቀናጀ የስኳር ልማት ፕሮጀክት ከዓመታት መጓተት በኋላ በተያዘው ግንቦት ስኳር ማምረት እንደሚጀምር አብመድ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ከ13 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ እየለማ ያለው የጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክት አሁንም ወደ ሥራ መግባት በሚያስችል ደረጃ ላይ አለመገኘቱን ከፕሮጀክቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አንተነህ አሰጌ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ በያዝነው ግንቦት የስኳር ምርት ለማምረት እቅድ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም በወረርሽኙ ምክንያት ለሥራ በቂ የሰው ኃይል ማስገባት አልተቻለም፡፡ በቂ የሰው ኃይል ማስገባት አለመቻል ደግሞ እቅዱን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማከናወን እንቅፋት መፍጠሩን ነው ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት፡፡

ከወረርሽኙ ጥንቃቄ ጎን ለጎን ደግሞ ለሥራው የሚያገለግሉ 96 ኮንቴነር የፋብሪካ ዕቃዎች መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡ የገባውን ዕቃ የሚተክሉ ቻይናውያን ባለሙያዎችም አዲስ አበባ ደርሰው ለ14 ቀናት በአስገድዶ ለይቶ ማቆያ እንደሚገኙና ገልጸዋል፡፡ ከ14 ቀናት በኋላ ወደ ፕሮጀክቱ በመግባት መደበኛ ሥራቸውን እንደሚያከናውኑም ጠቁመዋል፡፡
እናም እቅዱን ወደ ቀጣይ 2013 ዓ.ም ታኅሣስ ማራዘሙን ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን ፋብሪካው ስኳር ለማምረት ዝግጁ ቢደረግም ለምርት በቂ ስኳር አገዳ አለመኖር ደግሞ ሌላው ፈታኝ ጉዳይ መሆኑን አቶ አንተነህ ተናግረዋል፡፡ አሁን ፋብሪካው ስኳር ማምረት ቢጀምር ለምርቱ መሆን የሚችል አራት ሺህ ሄክታር ብቻ ስኳር አገዳ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ ‘‘ሌላው ስኳር አገዳ ግን ፋብሪካው በወቅቱ ባለመድረሱ በዕድሜ ብዛት ከጥቅም ውጭ ሆኗል’’ ብለዋል፡፡

ጣና በለስ የተቀናጀ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በቀን 10 ሺህ ኩንታል ማምረት እንደሚችል የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ ለዚህ ደግሞ 20 ሄክታር ስኳር አገዳ እንደሚያስፍልገውም ተናግረዋል፡፡

ለምርቱ አስፈላጊ አገዳ የሚደርሰው ደግሞ በቀጣይ ከሦስት እስከ አራት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለፕሮጀክቱ ሌላ ፈተና መሆኑን ነው ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት፡፡ ስኳር ለማምረት አጠቃላይ የግንባታ ሂደቱ 80 በመቶ መድረሱን ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

ፎቶ፡- ከድረገጽ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበተለያዩ ወንጀሎች ከተጠረጠሩ 97 ግለሰቦች መካከል 41 በሕግ ጥላ ስር መዋላቸውን ኮማንድ ፖስቱ ገለጸ፡፡
Next articleበመጪው የመኸር ወቅት ተጨማሪ ምርት ለማግኘት ከ60 ሺህ ሄክታር መሬት ለአልሚዎች ሊተላለፍ ነው፡፡