
አዲስ አበባ:ሚያዝያ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኪነ ጥበብ እና የሀገሪቱ ሚዲያ ባለሙያዎች ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካን ጎብኝተዋል። ለጉብኝቱ ተሳታፊዎች ማብራሪያ የሰጡት የኢስት አፍሪካ ናሽናል ዲስትሪቢውሽን ተወካይ አዳነ ዓለሙ ፋብሪካው ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሲሚንቶን ወደ ገበያ አቅርቧል ብለዋል።
ፋብሪካው መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት በሦስት ዓመታት ውስጥ የግንባታ ሥራውን ጨርሶ ወደ ምርት መግባቱ በሀገሪቱ የፕሮጀክት አፈጻፀም በተምሳሌትነት የሚጠቀስ ነው ሲሉ ገልጸዋል። የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ በአካባቢው ያለውን ሰላም በመጠቀም ምርቶችን በፍጥነት ወደ ገበያ ለማድረስ የተደረገው ጥረት ውጤታማ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ምርቶች ወደ ገበያ መግባት በጀመሩባቸው ባለፉት ስድስት ወራት በሲሚንቶ ገበያው ላይ ከፍተኛ መረጋጋት እና የዋጋ ቅናሽ ታይቷል ብለዋል፡፡ ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ በሲሚንቶ ምርት፣ በምርት ስርጭት እና መሠል የዕሴት ሰንሰለቶች በሺህ ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
በአዲስ አበባ፣ በለሚ እና በድሬዳዋ ከተሞች ልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ተግባራትን ማለትም የምገባ አገልግሎት፣ የትምህርት፣ የጤና እና የመኖርያ ቤት ግንባታዎችን፣ ልዩ ልዩ የትምህርት ዕድሎችን እና መሰል አገልግሎቶችን በማመቻቸት በዜጎች ጤናማ አኗኗር፣ በመሠረተ ልማት እና የትምህርት ዕድሎችን ማስፋት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉ የኪነ ጥበብ እና የሀገሪቱ ሚዲያ ባለሞያዎች ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካን በሀገሪቱ ዕድገት ላይ የራሱን አስተዋጽኦ የሚያደርግ ፋብሪካ መኾኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል። አርቲስት ችሮታው ከልካይ ፋብሪካው ግዙፍ እና ለሀገሪቱ የላቀ ፋይዳ እያበረከተ መኾኑን መመልከቱን ተናግሯል።
ኮሜዲያን በረከት በቀለ (ፍልፍሉ) በበኩሉ በየአካባቢው የሚገኙ እምቅ ሃብትን ማልማት ከተቻለ ከራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍ እንደሚቻል ማየቱን ነው ያስረዳው። የኪነጥበብ እና የሀገሪቱ ሚዲያ ባለሞያዎች ለፋብሪካው አምባሳደር ኾነው እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሃመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን