“ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና አካል ጉዳት”

33

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰውን ልጅ እና የዲጂታል አስተውሎትን አጣምሮ በመያዝ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) አሁን በደረስንበት ዘመን በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እና ውጤትም እያመጣ ይገኛል፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ላይ ላሉ የሰው ልጆች አስገራሚ እገዛዎችን እያደረገ ቢኾንም በተለየ ሁኔታ ደግሞ በአካል ጉዳተኞች የዕለት ከዕለት ሕይዎት ላይ ትርጉም ያለው አስተዋጽዖ እያደረገ ይገኛል፡፡

በተለያየ የአካል ጉዳት ዓይነቶች ላይ ላሉ ሰዎች የሰው ሠራሽ አስተውሎት ብዙ አማራጮችን አምጥቷል፡፡ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ድምጽን ወደ ጽሑፍ መቀየር በሚያስችል የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያ በመታገዝ የተባለው ነገር ምንድን ነው የሚለውን ለማወቅ ይችላሉ፡፡

ዐይነ ስውራን በዐይናቸው አይተው መረዳት የማይችሏቸውን ትዕይንቶች፣ ምስሎች እና አካባቢያዊ ሁኔታዎችን በሰው ሠራሽ አስተውሎት በመታገዝ ገለጻዎችን ለማግኘት ቀላል ይኾንላቸዋል፡፡ አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስቸግር የጤና እክል ያለባቸው ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ እና ቁሳቁሶችን ለማንሳት የሚቸገሩ ሰዎች የሰው ሠራሽ አስተውሎትን የተላበሱ ድጋፍ ሰጭ መሳሪያዎችን በመጠቀም ፍላጎታቸውን ማሟላት ይችላሉ፡፡

ለአብነት ባዮኒክ አርም በመባል የሚጠራው ሰው ሠራሽ እጅ በጭንቅላት ላይ በሚገጠም መቆጣጠሪያ ቺፕ (የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ) አማካኝነት በጉዳት ምክንያት እጅ የሌላቸው ወይም የተጎዳባቸው ሰዎች በእጅ የሚሠሩ ተግባራትን እንዲሠሩ ያግዛል፡፡

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ውጤቶች ሕይዎትን ለማቅለል ታስበው ቢዘጋጁም የአካል ጉዳተኞችን ችግር ግምት ውስጥ ያላስገቡ ሲኾኑ ለአካል ጉዳተኞች አስቸጋሪ ይኾንባቸዋል፡፡ ምክንያቱም በአካል ጉዳት ምክንያት ማከናወን ያልቻሉትን ተግባር እንዳያከናውኑ እክል ይኾንባቸዋል፡፡

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ውጤቶች የአካል ጉዳተኞችን በሚፈልጉት ልክ እንዲያግዙ ለማድረግ ከራሳቸው ከአካል ጉዳተኞች በቂ የኾነ መረጃ መውሰድ፣ ገበያ ላይ የዋሉ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ እና በአጠቃቀም ዙሪያ ጠንካራ ሕግ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡

ምንጭ፡- The AI Revolution: Is it a Game Changer for Disability Inclusion? | United Nations Development Programme

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleከ23 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየሠራ መኾኑን የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
Next articleከ12 ሚሊየን ኩንታል በላይ ስሚንቶ ወደ ገበያ ማቅረቡን ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፍብሪካ አስታወቀ።