ከ23 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየሠራ መኾኑን የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

28

ደብረ ብርሃን: ሚያዝያ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የ2017/18 የምርት ዘመን የመኸር ሰብል ልማት የንቅናቄ መድረክ እና የ9 ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በደብረ ታቦር ከተማ አካሂዶል።

በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ ዞኑ በበጋ መስኖ፣ በተፈጥሮ ሀብት ሥራ፣ በውኃ መሳቢያ ሞተር ስርጭት እና በግብዓት አቅርቦት የተሻለ ሥራ መሥራቱን አንስተዋል። አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያን በአግባቡ በመጠቀም ምርታማ እንዲኾኑ የባለሙያ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

አርሶ አደሮች ምርጥ ዘርን በመጠቀም እና በኩታ ገጠም በማረስ ተጠቃሚነታቸውን ከፍ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት።

የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ የሺጥላ ፈቃዴ ለመኸር ሰብል ልማት አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

በ2017/18 የምርት ዘመን በዞኑ ከ600 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዘር በመሸፈን ከ23 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት በእቅድ ተይዞ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ለስኬቱም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በንቅናቄ መድረኩ የተገኙት ተሳታፊዎች ለ2017/18 የምርት ዘመን ከአርሶ አደሮች ጋር የተቀናጀ ሥራ እየሠሩ መኾኑን አንስተዋል።

የፋርጣ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማድነው ብርሃን ምርጥ ዘር እና ግብዓትን በፍትሐዊነት እያቀረቡ መኾናቸውን ገልጸዋል። አርሶ አደሮችም ማሳን የማለስለስ ተግባሩን እያስኬዱ እና ቅድሚያ የሚዘሩትን ለመዝራት ዝግጅት እያደረጉ መኾናቸውን ተናግረዋል።

በሰዴ ሙጃ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ አበራ አስፌ ወረዳው ከፍተኛ የቦለቄ አምራች መኾኑን አንስተዋል። ለአርሶ አደሮች ተከታታይነት ያለው ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት በመስመር የመዝራት እና የኩታ ገጠም እርሻ ልምድን በማሳደግ ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleዘመናዊ የምርመራ ስልትን መጠቀም እና የሕግ መርሆችን በመከተል ማኅበረሰቡን ማገልገል እንደሚገባ ተጠቆመ።
Next article“ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና አካል ጉዳት”