
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕግ ባለሙያዎች ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት በዓለም አቀፍ ወንጀሎች ምርመራ እና ክስ አመሠራረት ላይ ለአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ አባላት ሥልጠና ሰጥቷል። የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ድርጅት የሥልታዊ ሙግት አሥተባባሪ ሜሮን ተስፋዬ እንዳሉት በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ጸድቋል። ፖሊሲውን ለማስፈጸም የተለያዩ ሕጎችም በረቂቅ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ድርጅትም ለሽግግር ፍትሕ ረቂቅ የሚኾኑ ግብዓቶችን እና ሥልጠናዎችን ሲሠጥ መቆየቱን ገልጸዋል። አሁን ላይም የሽግግር ፍትሕ ወደ ትግበራ ከመገባቱ በፊት ብቁ የኾኑ የፍትሕ ባለሙያዎችን ለመፍጠር ሥልጠና እየሠጠ መኾኑን ነው የተናገሩት። ሥልጠናው የፖሊስ አባላትን በዓለም አቀፍ ወንጀሎች ዙሪያ የምርመራ እና የክስ አመሠራር ሂደት ግንዛቤ የሚያሳድግ ነው።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው እንዳሉት የፖሊስ ተቋም በተለያዩ ግጭቶች የሚፈጠሩ ውስብስ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ምርመራ በማጣራት አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው።
በተለይም ደግሞ ውስብስብ እና ዓለም አቀፍ ባሕሪ ያላቸው እንደ ዘር ማጥፋት፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የጦር ወንጀል የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን ለመከላከል፣ ተፈጽመው ሲገኙ ደግሞ በአግባቡ ምርመራ በማካሄድ ወንጀለኞችን ለፍትሕ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም ለመገንባት ሥልጠናዎች አሥፈላጊ ናቸው።
አሁን የተሠጠው ሥልጠና የምርመራ ክፍተቶችን በመሙላት ለሕግ የበላይነት መከበር እና ለፍትሕ መረጋገጥ አቅም የሚፈጥር ነው። ከሥልጠናው በኋላ ዘመናዊ የምርመራ ዘዴዎችን በመጠቀም እና ዓለም አቀፍ የሕግ መርሆችን በመከተል ማኅበረሰቡን ማገልገል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊ ኢንስፔክተር ትዕግሥት መንገሻ ሥልጠናው በዓለም አቀፍ ወንጀሎች የምርመራ እና የክስ አመሠራረት ላይ አቅም የሚፈጥር ነው። የምርመራ ሂደትን ለማዘመን እና አገልግሎት አሠጣጡን ለማቀላጠፍ በሚወጡ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ሕጎች ላይ እስከ ታች ለሚገኙ ባለሙያዎች ሥልጠናዎችን ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ሌላኛው ተሳታፊ ኢንስፔክተር መለሰ አምባቸው እንዳሉት ሥልጠናው በየአካባቢው ከሚከሰቱ ወንጀሎች ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ የወጡ ሕግችን አውቆ እና ቀድሞ ለመከላከል፣ ወንጀሉ ከተከሰተ ደግሞ ለመከታተል እና ለመመርመር ያግዛል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!