መሪዎች የጤና መድኅን ቤተሰብ ምሥረታ አካሄዱ።

12

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎በአማራ ክልል የማኅበራዊ ዘርፍ መሪዎች የጤና መድኅን ቤተሰብ ምሥራታ ሥነ ሥርዓት አካሂደዋል። በምሥረታ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር ) የማኅበራዊ ዘርፍ የሥራ ኅላፊዎች ለሌሎች አርዓያ ለመኾን የጤና መድኅን ቤተሰብ መመሥረታቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን ጤና ለመታደግ ያስችላል ነው ያሉት። የማኅበራዊ ጉድኝት መሪዎች ለመነሻነት የ45 ቤተሰቦችን ወጭ በመሸፈን የጤና መድኅን ተጠቃሚ የሚያደርግ ቤተሰብ መመሥረቱን ገልጸዋል። ለእነዚህ ቤተሰቦችም የጤና መድኅን መጠቀም የሚያስችላቸውን ደብተር ማስረከባቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ የማኅበረሰብ ጤና መድኅን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለረጅም ዓመታት ተግባራዊ ሲኾን በመቆየቱ የማኅበረሰቡን ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል ሚናው ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ የጤና መድኅን በክልሉ የጤና ዋስትናን በማረጋገጥ የጤና አገልግሎቶችን ጥራት፣ ፍትሐዊነት፣ ተደራሽነት እና ዘላቂነት ለማረጋገጥ ቁልፍ ተግባር እንደኾነም አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ከፍተኛ መሪዎች፣ በጤና ሙያተኞች እና በማኅበረሰቡ ርብርብ 80 ነጥብ 1 በመቶ የሚኾነው የክልሉ አባዎራ እና እማዎራ የማኅበረሰብ ጤና መድኅን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። በአማራ ክልል የሚገኙ 23 የማኅበራዊ ክላስተር መሪዎች ገንዘብ በማዋጣት የማኅበረሰብ ጤና መድኅን ተጠቃሚዎችን ቤተሰብ መሥርተዋል፡፡ የእነዚህን ቤተሰቦች የጤና መድኅን በዘላቂነት ይዘን ለመዝለቅ በቁርጠኝነት እንሠራለንም ነው ያሉት፡፡

መልካም ሥራ ለራስ፣ ለቤተሰብ እና ለሀገር ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡ የጤና መድኅን ቤተሰብ አባል ከኾኑት መካከል አቶ ይትባረክ አያሌው የረጅም ጊዜ የመድኅኒት ተጠቃሚ በመኾናቸው በጤና መድኅን ቤተሰብ መታቀፋቸው ጥቅሙ ከፍ ያለ እንደኾነ ነው የተናገሩት፡፡

ወይዘሮ ስንዱ ታረቀኝ በበኩላቸው ብዙን ጊዜ የመታከሚያ ገንዘብ ስለሚያጡ ወደ ጤና ተቋም ሂደው ለመታከም እንደሚቸገሩ ገልጸዋል። ከዚህ በኋላ ግን በጤና መድኅን ደብተራቸው እስከ ቤተሰባቸው መታከም እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየከተማ ግብርና የአመጋገብ ሥርዓትን እያሻሻለ ነው።
Next article“ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ለቻይናውያን ባለሀብቶች ምቹ ናት” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ