
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ ግብርና በአነስተኛ ቦታ ዘመናዊ አሠራር እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለምግብነት እና ለሌሎች ጠቀሜታዎች የሚውሉ የግብርና ምርቶችን ማቅረብ የሚያስችል ዘርፍ ነው፡፡ አሠራሩ በተለያዩ ቦታዎች የሚከናወን ሲኾን በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ሚናው ከፍተኛ እንደኾነ የዘርፍ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በ2017 በጀት ዓመት በድግግሞሽ የተሳተፉትን ጨምሮ በመስኖ ብቻ ከ14 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ከከተማ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ከተሳታፊዎች ውስጥ መሪጌታ ግዛቸው ሞላ አንዱ ናቸው። በከተማ አሥተዳደሩ በመስኖ ልማት ከተሠማሩ አስር ዓመታትን እንዳስቆጠሩ ተናግረዋል። በአንድ ሄክታር መሬት የተጀመረው ልማት አሁን ላይ በሦስት ሄክታር መሬት ላይ አትክልት እና ፍራፍሬ እያለሙ ይገኛሉ።
በዓመት ሁለት ጊዜ በማምረት ለከተማው ማኅበረሰብ እያቀረቡ እንደኾነ መሪጌታ ግዛቸው ገልጸዋል። በግብርና ምክረ ሀሳብ መሠረት በመሥራታቸው የተሻለ ምርት እያገኙ እንደኾነም ገልጸውልናል። ለአራት ሰዎችም የሥራ ዕድል ፈጥሬያለሁ ነው ያሉት። የተሻለ ኑሮ እየኖሩ መኾኑንም ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ ባለሙያ ሞላልኝ መንግሥቱ በ2017 በጀት ዓመት በከተማ አሥተዳደሩ 4 ሺህ 893 ሄክታር መሬት በአንደኛ ዙር በመስኖ ለምቷል ብለዋል።
በዘርፉ በድግግሞሽ የተሳተፉትን ጨምሮ ከ14 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ወደ ልማት መግባታቸውንም ነግረውናል።
ስንዴ እና ጤፍ የመሳሰሉ ሰብሎች፣ ከአትክልት እንደ ቀይ ሽንኩርት፤ ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ ቆስጣ፣ ሰላጣ፣ እና ጥቀል ጎመን፤ ከፍራፍሬ ደግሞ ሀብ ሀብ፣ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ዘይቱና፣ ሙዝ እና ቡና የመሳሰሉት ላይ በትኩረት ተሠርቷል ብለዋል። እስከ አሁንም 304 ሺህ 534 ኩንታል ምርት መገኘቱን ነው የገለጹት።
ለከተማ ግብርና በተሠጠው ትኩረት ማኅበረሰቡ ምርት በቅርብ እንዲያገኝ ተደርጓል ነው ያሉት። በተለይም አትክልት እና ፍራፍሬ ምርት የያዘውን ንጥረ ነገር ሳያጣ በትኩሱ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል። ማኅበረሰቡም የአመጋገብ ሥርዓቱን በማሻሻል ጤናውን እንዲጠብቅ ዕድል ፈጥሯል ነው ያሉት።
የሚመረተው ምርት ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ ማቆየት የሚችል ቴክኖሎጅን ማስፋት ከተቻለ ደግሞ ምርቱን በዘላቂነት ለገበያ በማቅረብ ማኅበረሰቡን እና አምራቹን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!