“የሃሳብ ልዩነት በወንድማማችነት እና በመነጋገር ብቻ መፈታት አለበት” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

40

አዲስ አበባ: ሚያዝያ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአቶ ግርማ የሺጥላ የ2ኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ መርሐ ግብር በመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማዕከል እየተካሄደ ነው።

2ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ መርሐ ግብሩን አስመልክቶም በመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማዕከል ለሚገኙ ከ8 ሺህ በላይ አረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን ማዕድ አጋርተዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ቤተሰቦቹ፣ የተለያዩ የሥራ ኀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የጧፍ ማብራት ሥነ ሥርዓትም ተካሂዷል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የአቶ ግርማ ሞት የሃሳብ ልዩነትን በግድያ ለማጥፋት የተደረገ የፅንፈኝነት ማሳያ ነው ብለዋል። “የሃሳብ ልዩነት በወንድማማችነት እና በመነጋገር ብቻ መፈታት አለበት” ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ.ር) የሥራ አጋር ኾነው በቆዩባቸው ጊዜያት አቶ ግርማ የሺጥላ ደፋር፣ ለያዘው ዓላማ በፅኑ የሚታገል እና ስለኢትዮጵያ የሠራ እውነተኛ ሰው ነበርም ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ አቶ ግርማ ለአማራ ሕዝብ ጥቅም የታገለ፣ ከፍ ሲልም ለኢትዮጵያ እድገት የሠራ ጥሩ አቅም የነበረው ጠንካራ መሪ እንደነበር ጠቅሰዋል።

የአማራን ሕዝብ ሰላም በመመለስ ትግሉን ከዳር ማድረስ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሽ አለማየሁ አቶ ግርማ የሺጥላ ልማት፣ ዴሞክራሲ እና ፍትሕ እንዲረጋገጥ አበክሮ ሠርቷል ብለዋል። ዞኑ ላይ አሁን እየታዩ ያሉት ለውጦች የእሱ አበርክቶ ማሳያ መኾናቸውንም አንስተዋል።

የአቶ ግርማ የሺጥላ ባለቤት ወይዘሮ ሠርክዓለም መላኩ ለእርስ በእርስ ጦርነት የሚከፈል መስዋዕትነት ሊቆም እና ባለቤታቸው በፅኑ የታገለለትን ሰላም ማምጣት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

አቶ ግርማ የሺጥላ ሚያዝያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም በሥራ ላይ እያሉ ከታጣቂዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ቴሌብር ለአካታች እና ተደራሽ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው” ፍሬሕይወት ታምሩ
Next articleየከተማ ግብርና የአመጋገብ ሥርዓትን እያሻሻለ ነው።