
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ከቪዛ ኢንክ የደቡብ እና ምሥራቅ አፍሪካ ሪጅኖች ምክትል ፕሬዝዳንት ሚካኤል በርነር ከሚመራ የልዑካን ቡድን ጋር በዓለም አቀፍ የዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶች ላይ አዳዲስ የትብብር ዕድሎችን ለመፈተሽ የሚያስችል ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ነሐሴ 2016 ዓ.ም በጋራ ይፋ ያደረጉት በሀገሪቱ የመጀመርያው የዋሌት ቨርቹዋል ቪዛ ካርድ፣ በቪዛ ዳይሬክት እና በቴሌብር ረሚት በኩል የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ሐዋላ አገልግሎቶች የሚገኙበት ደረጃ ቀርቧል።
በሐዋላ አገልግሎቶቹ የተመዘገበው አበረታች አፈጻጸም፣ ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ እያደገ በመጣው የገበያ ዕድል እና የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በዓለም አቀፍ ሐዋላ አገልግሎቶች ላይ ቀጣይነት ያለው ማሻሻያ እየተከናወነ መሆኑ ተብራርቷል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ቴሌብር ለአካታች እና ተደራሽ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ቴሌብርን ከቪዛ ዓለም አቀፍ ኔትወርክ ጋር በመጣመር አዳዲስ ፈጠራ የታከለባቸው የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ማቅረብ የሚቻልበት ዕድሎች መኖሩን አብራርተዋል።
የቪዛ ኢንክ የልዑካን ቡድን በጋራ ተግባራዊ የተደረጉት ዓለም አቀፍ አገልግሎቶች ስኬት በማድነቅ የገበያውን ከፍተኛ ጥቅም ላይ ያልዋለ አቅም መጠቀም እንደሚገባ አመላክተዋል።
ከኢትዮ ቴሌኮም የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ተጨማሪ የትብብር ዕድሎችን በመፈተሽ የፋይናንስ ተደራሽነትን የሚያሰፋና በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ባሕል ግንባታ ላይ ጉልህ አሻራ ለማኖር ተቀራርቦ የሚሠራ የጋራ ቡድን ለማቋቋም ተስማምተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!