የመንግሥት ሠራተኞች የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶችን በማስተካከል በቅንነት ሊያገለግሉ እንደሚገባ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አሳሰበ።

35

ጎንደር: ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር” አገልግሎት አሰጣጤን በማሻሻል እና ብልሹ አሠራርን በማስወገድ ከተማዬን እክሳለሁ ” በሚል መሪ መልዕክት ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የመንግሥት ተቋማት እየሰጡት ያለውን አገልግሎት አወንታዊ እና አሉታዊ ሂደት የሚያሳይ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ የመንግሥት ሠራተኞች ከማኅበረሰብ የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶችን በማስተካከል በቅንነት ሊያገለግሉ እንደሚገባ አሳስበዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ መኮንን በአግባቡ አገልግሎት የሚሠጡ ተቋማት እና የመንግሥት ሠራተኞችን በማበረታታት ክፍተት የሚፈጥሩትን ማስተካከል ይገባል ብለዋል።

ለማኅበረሰቡ የተሟላ አገልግሎት በመሥጠት የከተማውን ዘላቂ ሠላም እና ልማት ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት መምሪያ ኀላፊ ነፃነት መንግሥቴ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን በመተግበር መንግሥት ሠራተኞች ተገቢውን አገልግሎት ለማኅበረሰቡ እንዲሠጡ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

የከተማዋ ከፍተኛ መሪዎች ለጉዳዩ ትኩረት ሠጥተው የማኅበረሰቡን ቅሬታ ለመፍታት እየሠሩ እንደኾነም ጠቁመዋል። አንዳንድ ተቋማት ላይ በተገቢው መንገድ አገልግሎት የማይሰጡ ባለሙያዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እየወሰዱ መኾናቸውን አስታውቀዋል። በቀጣይም ክፍተት ያለባቸውን የመንግሥት ሠራተኞች ከመደገፍ እና ሥልጠና ከመሥጠት ባሻገር ተጠያቂነት ይረጋገጣል ብለዋል።

የውይይቱ ተሣታፊ የመንግሥት ሠራተኞች በከተማው አገልግሎት አሰጣጡ ሕዝቡ በሚፈልገው መጠን አለመኾኑን ተናግረዋል። በቀጣይ በአግባቡ ለማገልገል ውይይቱ ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል። ማኅበረሰቡም አገልግሎትን በገንዘብ ለመግዛት ከመፈለግ ይልቅ መብቱን ለማስከበር መቆም እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ :- አገኘሁ አበባው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለዘላቂ እና ለአዎንታዊ ሰላም መረጋገጥ የላቀ ሚናን መወጣት ይገባል” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next articleየአማራ ክልል ምክር ቤት በተዋረድ ከሚገኙ የምክር ቤት አካላት ጋር የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው።