
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዘጠኝ ወራት የፖለቲካ እና የአደረጃጀት ሥራዎች አፈፃጸምን ገምግሟል።
በግምገማ መድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ፖለቲካዊ ስክነትና እና ብስለት፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ማኅበራዊ መረጋጋት ለሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዟችን ትክክለኛ ሀዲዶች ናቸው ብለዋል።
ገጥመውን የነበሩ የሰላምና ጸጥታ ችግሮች፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ስብራቶች ደረጃ በደረጃ እየተጠገኑ ሁለንተናዊ የብልጽግና መንገድ ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።
እስካሁን የሄድንባቸው የሰላምና የሕግ ማስከበር እና የልማት እንቅስቃሴዎች አዎንታዊ ለውጦችን እያመጡ ናቸው ያሉት ኀላፊው የክልሉ የሰላም ሁኔታ በከተማና በገጠር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል፡፡ አመርቂ የልማት ክንውኖችም ተጨባጭ ለውጦችን እያመጡ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ ባሳለፋቸው ውሳኔዎች እና ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
ለዘላቂ እና ለአዎንታዊ ሰላም መረጋገጥ የላቀ ሚናን መወጣት፣ የብሔራዊነት ገዥ ትርክት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ምሰሶ በመሆኑ በጥልቀትና በስፋት መረዳትና ማስረዳት፣ እያንዳንዱ ተግባርና ውጤቱ ጠንካራ ፓርቲና ጠንካራ መንግሥት፣ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት በሚያግዝ አግባብ ሊከወን ይገባል ነው ያሉት።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተመዘገቡ ድሎችን፣ የተገኙ ትሩፋቶችንና ስኬቶችን ማስጠበቅና ማጠናከር፣ በሂደቱ በአጋጠሙ ስህተቶች ላይ ትምህርት መውሰድና ፈጥኖ ማረም እንደሚገባም አመላክተዋል።
ከአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የሕዝባችንን ሁለንተናዊ መሻት ለማሟላት፣ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና አመርቂ ልማቶች እንዲጠናከሩ በቀሪ ወራት በጊዜ የለንም ስሜት መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን