
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከአማራ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈናቅለው የነበሩ 9 ሺህ 688 የኅብረተሰብ ክፍሎች መመለሳቸውን ኮማንድ ፖስቱ ገልጧል፡፡
በአማራ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በአዋሳኝ አካባቢዎች የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የአንድ ወር የተግባር አፈጻጸም ግምገማ በግልገል በለስ ከተማ ትናንት አካሂዷል። በግምገማው እንደተገለጸው ከአካባቢዎቹ ተፈናቅለው የነበሩ 9 ሺህ 688 የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል፡፡
የኮማንድ ፖስቱ አባል እና የክልሉ የሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አበራ ባየታ እንደገለጹት በስርቆት ተወስደው የነበሩ 581 የቁም እንስሳትም በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አማካኝነት ለባለቤቶች ተመልሰዋል፡፡ የፀጥታ ችግር ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 97 ግለሰቦች እንደተለዩ ያሳወቁት አቶ አበራ ማስረጃ ከተገኘባቸው 71 ሰዎች ውስጥ 41 በሕግ ጥላ ስር መዋላቸውንም ገልጸዋል፡፡
ኮማንድ ፖስቱ እንደአዲስ ተዋቅሮ ባደረጋቸው ክትትሎች በአንድ ወር ውስጥ 34 ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች እና 9 ሺህ 681 ቀስቶች በቁጥጥር ሥር ማዋሉንም አቶ አበራ ገልጸዋል። ከሁለቱም ክልሎች ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን የማስመለሱ ሥራ መጀመሩም በወሩ ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ በዚህም 9 ሺህ 688 የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን በመግለጽ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል፡፡
ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ለሚገኙት ዜጎች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍም መቀጠሉንም አቶ አበራ አስታውቀዋል፡፡ ተፈናቃይ ወገኖች በተደጋጋሚ የሚነሱትን የሰላምና ደኅንነት ዋስትናን በተመለከተም ኮማንድ ፖስቱ እንዲሁም ከክልል እስከ ቀበሌ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ኃላፊዎች ኃላፊነት የሚወስዱበት አሠራር መጀመሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ኅብረተሰቡን የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ግንዛቤ እየተፈጠረ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
ከመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ተፈናቅለው በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ተጠልለው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በዚህ ሳምንት ለማስመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም የኮማንድ ፖስቱ አባል እና የክልሉ የሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አበራ ባየታ አስታውቀዋል፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ከሚገኙ ከ120 ሺህ በላይ ዜጎች ውስጥ ከ49 ሺህ የሚልቁት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ እንደሆኑ ይታወሳል፡፡
መረጃውን ከግልገል በለስ ያደረሰን አማኑ ፋንታሁን ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡