ማኅበረሰቡ ነገን በማሰብ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን መጠበቅ አለበት።

25

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰሞኑ ብርቅዬ እንስሳው ዋልያ ላይ ግድያ የፈጸሙ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የሰሜን ጎንደር ዞን አስታውቋል።

የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኝ ድንቅ ሥፍራ ነው። በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ፓርኩ ጎብኝዎችን ወደ ኢትዮጵያ ከሚስቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል ቀዳሚው ነው። በፓርኩ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት ደግሞ የጎብኝዎችን ቀልብ በመሳብ ይታወቃሉ።

ፓርኩ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በቱሪዝም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ከሰሞኑ በስሜን ተራራዎች ፓርክ በሚገኘው የዋልያ ብርቅዬ እንስሳት ላይ ግድያ መፈጸሙ ይታወሳል።

ግድያው የብርቅዬ እንስሳቱን አደጋ ላይ የሚጥል እና በቱሪዝም እንቅስቃሴውም አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥር ነው።

የሰሜን ጎንደር ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ዳኝነት ሙሉሰው የአካባቢውን የጸጥታ ኀይል ከፓርክ ጥበቃ (ስካውት) ጋር በማቀናጀት የጥበቃ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

ከሰሞኑ እንደተፈጠረው አይነት ድርጊት እንዳይፈጸም እየሠሩ መኾናቸውን ነው ያመላከቱት። ዋልያዎችን ከገደሉ አካላት መካከል የተያዙ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን የተናገሩት ኀላፊው ቀሪዎችን ለመያዝ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ተጠርጣሪዎችን ለሕግ ከማቅረብ ጎን ለጎን የፓርኩን ደኅንነት ለመጠበቅ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል። ድጋሜ ችግር እንዳይፈጠር የተጠናከረ ጥበቃ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ከሰሞኑ በዋልያዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ ማኅበረሰቡ እያወገዘው ነው ያሉት ኀላፊው ከዚህ በላይ ማውገዝ እና ጥበቃውን ማጠናከር አለበት ነው ያሉት። የአካባቢው ማኅበረሰብ ለዘመናት ሲጠብቀው እንደኖረ እና እዚህ እንዳደረሰውም ነው የተናገሩት።

ለዘመናት ሲጠብቀው የኖረውን ፓርክ አጠናክሮ መጠበቅ እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ በፓርኩ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል ያሉት ኀላፊው በጸጥታ ችግር ምክንያት የጎብኝዎች ቁጥር ቀንሶ ቆይቷል፣ ይህ ደግሞ ማኅበረሰቡ ሲያገኝ የነበረውን ጥቅም በሚፈልገው ልክ አላገኝም፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከፓርኩ የሚያገኘው ጥቅም ሲቀንስ ደግሞ ለፓርኩ ጥበቃ የሚሰጠው ትኩረትም አብሮ ይቀንሳል ነው ያሉት።

ፓርኩ የአካባቢው ማኅበረሰብ በቱሪዝም እና በኢንቨስትመንት ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። ፓርኩን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ልዩ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ አስቸጋሪ ጊዜ ቢገጥም እንኳን ፓርኩ የሚኖረውን ዘላቂ ጥቅም በማሳብ ጥበቃውን ማጠናከር አለበት ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ የእኔ ነው ብሎ ጥበቃውን ካጠናከረ ችግሩን መቆጣጠር ይቻላል ብለዋል።

በዋልያዎች ላይ ግድያ ከተፈጸመበት ቀን ጀምሮ ጥበቃ እና ክትትሉ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አንስተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት የአርሶ አደሮችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግ ተገለጸ።
Next articleበኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚሳተፉ የሀገር አቀፍ እና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጥሪ እየቀረበላቸው ነው ።