የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት የአርሶ አደሮችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግ ተገለጸ።

32

አዲስ አበባ: ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓትን ለማጠናከር እና ለማስፋፋት በሚያስችሉ ጉዳዮች ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። ባለፉት ዓመታት የግብርናው ዘርፍ የምግብ እህል ፍላጎትን ከማሟላ ባሻገር ከፍተኛ የገቢ ምንጭ በመኾን ለኤክስፖርት እና ለኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የሚደረገውን መዋቅራዊ ሽግግር በመደገፍ እና በማሳለጥ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ሚና ሲጫወት እንደነበር የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስትር ድኤታ ያስሚን ወሀብረቢ አስታውሰዋል።

ይኹን እንጅ በዘርፉ የሚስተዋለው ረጅም የግብይት ዕሴት ሰንሰለት ለምርት ብክነት እና ጥራት መጓደል በወጭ ንግድ አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ነው የተናገሩት። በተለይም ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ጥሬ እቃ በጥራት እና በብዛት ለማግኘት መቸገር፤ የሀገር ውስጥ ገበያ ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም፣ አርሶ አደሩ በብዙ ድካም ያመረተውን ምርት የሚያስቀምጥበት በቂ የመጋዘን አገልግሎት እና የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር ችግር እንደነበር ጠቁመዋል።

ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት በጥራት፣ በብዛት እና በአይነት ከማቅረብ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ ገበያ የምርት ፍላጎት እና አቅርቦትን ለማመጣጠን እንዲቻል የግብይት እሴት ሰንሰለቱን ማዘመን እና የፋይናንስ አቅርቦትን ማመቻቸት ተቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል ሚኒስትር ድኤታዋ። የግብይት ሥርዓቱን ዲጅታላይዝድ ማድረግ ከሚያስችሉ አሠራሮች አንዱ በ2014 ዓ.ም ተግባራዊ የተደረገው የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት ነው ብለዋል።

ይህም ደግሞ የአርሶ አደሮችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ፕሮጀክት እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት። የዕቃ መጋዝን ደረሰኝ ሥርዓት አገልግሎት ፕሮጀክት ዋና ዓላማ አርሶ አደሮች ያመረቱትን ምርት በማስያዥነት በመጠቀም ከፋይናንስ ተቋማት የሚፈልገውን የብር መጠን የሚበደርበት ሥርዓት ነው ብለዋል።

እስካኹን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ አምሥት ባንኮች በመጋዝን ደረሰኝ ሥርዓት ተካተው የብድር አገልግሎት እየሠጡ መኾኑንም ሚኒስትር ድኤታዋ ገልጸዋል። በዚህም ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን አንስተዋል።

እስካኹን ግማሽ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት በማስያዣነት ጥቅም ላይ የዋለ ሲኾን ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ ብር 141 አምራች አርሶ አደሮች የብድር ተጠቃሚ መኾናቸውን ሚኒስትር ድኤታዋ አረጋግጠዋል።

የዕቃ ማከማቻ መጋዝን ደረሰኝ ሥርዓትን ለማጠናከር እና ለማስፋትም ባለድርሻ አካላት በርብርብ ሊሠሩ እንደሚገባ ተመላክቷል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleግብርን በታማኝነት በመክፈል ለከተማዋ ዕድገት አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደኾነ ምሥጉን ግብር ከፋዮች ተናገሩ።
Next articleማኅበረሰቡ ነገን በማሰብ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን መጠበቅ አለበት።