
ደሴ:ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ “ግብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ መልዕክት የዕውቅና እና የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል። መምሪያው በ2017 ዓ.ም ከ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሠብሠብ አቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ መሠብሠብ መቻሉን የደሴ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ መላኩ ሚካኤል ተናግረዋል።
በቀሩት ወራት በተቀናጀ መንገድ ገቢ በመሠብሠብ የ2017 ዓ.ም ዕቅዱን ለማሳካት በንቅናቄ እንደሚሠሩም ኀላፊው ገልጸዋል። ደሴ ከተማ የጀመረችው የልማት ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ግብር የጀርባ አጥንት በመኾኑ ግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ግብሩን በታማኝነት እና በወቅቱ በመክፈል ለከተማዋ ዕድገት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥልም የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ተናግረዋል።
በክልሉ በ2017 ዓ.ም ከ71 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሠብሠብ ታቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሠብሠቡን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኀላፊ የኔሰው መኮነን ናቸው። ”ምሥጉን ግብር ከፋይ መኾን ትልቅ ክብር ነው” ያሉት ምክትል ኀላፊው በበጀት ዓመቱ የታቀደውን ገቢ ለመሠብሠብ በቀሪ ወራት በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ግብር ከፋዩ ባለበት ኾኖ ግብሩን መክፈል እንዲችል እና ግብር ለመክፈል የሚገጥመውን እንግልት ለማስቀረት በሙከራ ላይ የሚገኘው ኢ-ታክስ ፕሮጀክት በክልሉ ተግባራዊ እንደሚደረግም ተገልጿል። ግብርን በታማኝነት መክፈላቸው ለከተማቸው ዕድገት አስተዋጽኦ ከማበርከት ባለፈ ትልቅ የሕሊና እርካት እንደሚሰጣቸው ምሥጉን ግብር ከፋዮች ተናግረዋል።
በንቅናቄ መድረኩ ለምሥጉን ግብር ከፋይ ግለሰቦች እና ለገቢ ሥብሠባው አስተዋጽኦ ላበረከቱ ክፍለ ከተማዎች ብሎም ተቋማት ዕውቅና ተሰጥቷል።
ዘጋቢ:- ሀያት መኮን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን