
ደባርቅ:ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች ጽሕፈት ቤት የዘንድሮው ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነፃፀር ዕድገት ማሳየቱን ገልጿል።
አጋዥ የቴክኖሎጅ አማራጮችን በመጠቀም ግልጽ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ እንደሚገኝም ነው የተብራራው።
የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብሬ ያለው የዚህ ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም አንፃር ሲታይ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ማሳየቱን ገልጸዋል። ዕድገቱ በመቶኛ ሲሰላም ከስምንት በመቶ በላይ መኾኑን አንስተዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከታቀደው ዕቅድ በመደበኛ ገቢ ከ75 በመቶ በላይ ግብር መሠብሠብ መቻሉንም አብራርተዋል።
በመደበኛ ገቢ እና በአገልግሎት ገቢ ከ58 በመቶ በላይ ግብር መሠብሠብ መቻሉን ጠቅሰዋል።
ግልጽነት እና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የቴክኖሎጅ አማራጮችን በመጠቀም አሠራሩን ለማዘመን እየተሠራ እንደሚገኝም አቶ ገብሬ አንስተዋል።
በደረጃ ‘ሀ’ እና ‘ለ’ ግብር ከፋዮች ሲተገበር የቆየውን በቴክኖሎጅ የታገዘ አሠራር በደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮችም ተጀምሯል ብለዋል።
በወቅታዊ የሰላም ሁኔታው ምክንያት የሚፈለገውን ያክል የአፈፃፀም መሻሻል ለማስመዝገብ ባይቻልም ጫናውን በመቋቋም እየሠሩ ስለመኾኑ አስገንዝበዋል።
የማኅበረሰቡን የልማት ጥያቄ መመለስ የሚቻለው ግብር በአግባቡ መሠብሠብ ሲቻል በመኾኑ ኅብረተሰቡ በግብር አሠባሠብ ሂደቱ ላይ ትብብር ሊያደርግ ይገባልም ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን