
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ ሳይንስ እና አይሲቲ ሚኒስቴር ስር የሚገኘው የኮሪያ ኢንፎርሜሽን ሶሳይቲ ልማት ኢንስቲትዩት (KISDI) ጋር መክሯል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ድኤታ ይሹሩን ዓለማየሁ (ዶ.ር) በስታንዳርድ ፖሊስና በኤሌክትሮኒክስ ንግድ የሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ በቀረበ የፕሮጀክት ፕሮፖዛል መሠረት የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ስነ ምኅዳር የሚደግፉ እና የሚያሻሽሉ ሀገራዊ ደረጃዎችን፣ ፖሊሲዎችን እና መመሪያዎችን ለማዘጋጀት ድጋፍ ለማድረግ ከመጡ ከፍተኛ የአማካሪዎች ቡድን ጋር መክረዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ድኤታ ይሹሩን ዓለማየሁ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ እና የደቡብ ኮሪያ መንግሥት እና ሕዝብ የቆየ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው በመኾናቸው በበርካታ በይነ መንግሥታዊ ትብብሮች ግንኙነታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን አውስተዋል። የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ኢትዮጵያን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ልማት እንድትጠናከር ለሚያደርገው ድጋፍም አመስግነዋል፡፡
የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ኢትዮጵያን በዲጅታል ትራንስፎርሜሽን የምታደርገውን ጥረት እያገዘ መኾኑንም ገልጸዋል። ‘’የኤሌክትሮኒክ ንግድ ሥርዓትን በላቀ ደረጃ መተግበር እና መጠቀም የሚያስችል አሠራር እንዲዘረጋ በትኩረት እየተሠራ ነው ‘’ያሉት ሚኒስትር ድኤታው አማካሪ ድርጅቱ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የኤሌክትሮኒክ ንግድ (ኢ ኮሜርስ) ወጥነት ያለው፣ ማነቆዎችን የሚፈታ እና በተገልጋዩና ተጠቃሚው ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት አጥንቶ በማቅረብ እንዲተገበር፣ ተግዳሮቶችን እንዲፈታና ከዳበረው ዓለማቀፍ የኤሊክትሮኒክ ንግድ ሥርዓት ጋር ለማስተሳሰር አቅም ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአሁኑ ከ80 ሚሊዮን በላይ ሞባይል ስልክ ተጠቃሚ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የሚገኝ የኢንተርኔት ተደራሽነትና ሽፋን መኖር፣ የዲጅታል መታወቂያ አገልግሎት መስፋፋት በመኖሩ የኤሌክትሮኒክ ንግድን ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ ለተግበርና ለአህጉራዊና ቀጣናዊ ትስስሩን ለማስፋት በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የቡድኑ ውጤት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ኅብረት አባልነት፣ ለአህጉራዊ የንግድ ትስስር ትልሟና ለዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ለምታደርገው ጉዞ አሠራሩን ወጥነት እንዲኖረው የሚያደርግ ነው።
ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በመስኩ ያጋጠሙትን ችግሮች እና ማነቆዎችን ለመፍታት የሚያስችል መፍትሔ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን