የኢንዱስትሪ እና ፋይናንስ ኤክስፖ ዝግጅት መጠናቀቁን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

42

ደሴ:ሚያዝያ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “የኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” አካል የኾነው በኮምቦልቻ ከተማ ከሚዚያ 20 እስከ ሚያዚያ 30 2017 ዓ.ም ለሚካሄደው የኢንዱስትሪ እና ፋይናንስ ኤክስፖ ዝግጅት መጠናቀቁን ከተማ አሥተዳደሩ አስታውቋል።

የቀጣናውን እምቅ የመልማት አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተውን የኢንዱስትሪ እና የፋይናንስ ኤክስፖ ለማካሄድ ጥቂት ቀናት ቀርተዋል። ኤክስፖው “ሰላም የኢንቨስትመንት ፓስፖርት ነው” በሚል መልእክት እንደሚካሄድ ነው የተገለጸው።

አሚኮም ለሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪ እና ዩፋይናንስ ኤክስፖው ማኅበረሰቡ እና ኮሚቴው ያደረጋቸውን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

አስተያየታቸውን የሰጡን በተለያዩ አገልግሎት ዘርፎች የተሰማሩ የከተማዋ ነዋሪዎችም ለኤክስፖው መሳካት እና እንግዶችን ለመቀበል ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ እና የወሎ ኮምቦልቻ ሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪ እና የፋይናንስ ኤክስፖ ኮሚቴ ምክትል ሠብሣቢ ሁሴን ሙሔ የተቋቋሙት ንዑሳን ኮሚቴዎች ኀላፊነታቸውን መወጣታቸውን ገልጸዋል። ለእንግዶችም ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ነው ያሉት።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወንድወሰን ልሳነወርቅ ኤክስፖው ከተማዋን የበለጠ ለማዘመን አዳዲስ አሠራሮች እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ከፍ ለማድረግ ልምድ የሚወሰድበት ነው ብለዋል።

ከ200 በላይ ሀገር አቀፍ እና ዓለምአቀፍ ኢንዱስትሪዎች ምርት እና አገልግሎታቸውን እንደሚያስተዋውቁም አመላክተዋል።

በርካታ የፋይናንስ ተቋማት በኤክስፖው እንደሚሳተፉም ተገልጿል። አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለዕይታ ይቀርባሉ ነው የተባለው። ተቋማቱ ተኪ ምርት እንዲያመርቱ የሚበረታቱበት ሁነት እንደኾነ ነው የተናገሩት።

ዩኒቨርሲቲዎች እና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የምርምር ሥራወቻቸው እና የቴክኖሎጂ ውጤቶቻቸውን ያቀርባሉ ያሉት ምክትል ከንቲባው የከተማዋን የወደፊት የመልማት ዕድል የሚወሰኑ ውይይቶች ይካሄዳሉ ነው ያሉት።

የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችም በሁሉም ዘርፍ መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡም የተለመደውን የእንግዳ ተቀባይነት እሴቱን በተግባር እንዲያሳይ አሳስበዋል።

ዘጋቢ ፦ አንተነህ ፀጋዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየደሴ ከተማ አሥተዳደር የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ አጋርቷል።
Next articleየኤሌክትሮኒክ ንግድ ሥርዓትን በላቀ ደረጃ መተግበር የሚያስችል አሠራር እንዲዘረጋ በትኩረት እየተሠራ ነው።