
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) “ልጆቼ በድህነቴ ላይ ቸርነትን አድርጉልኝ፡፡ በዚህ አልችልም ካላችሁ በቁስሌ ላይ ዘይትን አፍስሱልኝ፡፡ አሁንም ይሄን ማድረግ ካልቻላችሁ ወደእኔ ጠጋ በሉና አናግሩኝ፡፡ እናንተን ማዬት ከእናንተ ጋር መጫዎት ይናፍቀኛል፡፡” የአረጋውያን፣ የሕጻናቱና የአዕምሮ ሕሙማኑ ጥሪ ነው፡፡ ለካስ ምግብ ብቻ አይደለም የሚርበው፤ ለካስ ውኃ ብቻ አይደለም የሚጠማው ሰውም እንደ እህል ውኃ ይርባል፤ ይጠማል፡፡
ዕድሜያቸው ገፍቶ ሲርብ የሚያጎርስ፣ ሲያልቅ የሚያለብስ ጧሪ ያጡ፣ ወላጆቻቸውን በጠዋት የተነጠቁና ኖረውም ማሳደግ የማይችሉ ወላጆች ያሏቸው ሕጻናትና የአዕምሮ ሕሙማን በአንድ ማኅበር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ያ ማኅበር በጎነትን ማሳያ መስታውት ነው፡፡ ገሚሶቹ ራሳቸውን በዚያ ውስጥ ማግኘታቸው አሳዝኗቸው ይመስላል በቁዘማ ተቀምጠው በትዝታ ጭልጥ ብለዋል፡፡ ገሚሶቹ የአዕምሯቸው ሕመም አይሎባቸው ሳር ቅጠሉን ያስጨብጣቸዋል፤ ያስጮኻቸዋል፤ ከተለያየ የማኅፀን ምንጭ የተገኙ በደግነት ጥላ ስር የተገናኙ ሕፃናት ደግሞ በአጥሩ ዙሪያ ሲላፉ ይታያሉ፡፡
ክፍያቸውን ከፈጣሪ ብቻ የሚጠብቁ በጎ አድራጊ ወጣቶች ደግሞ ያለማቋረጥ ለመልካም ተልዕኮ ይፋጠናሉ፡፡ ነገሩ ሁሉ ልብ ይሰርቃል፡፡ በዚያ ግቢ ውስጥ የደረሱ ሁሉ ማዘናቸው እና ማንባታቸው የሚቀር አይመስልም፡፡ እነዚያን ሰዎች ያሰባሰቧቸው ሁሉ የራሳቸውን ሕይወት ለሰው የሰጡ፤ የጭንቅ ቀን መሰላል፣ የጨለማ መውጫ ሻማም ናቸው፡፡
በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ጯኂት ከተማ ላይ የሚገኘው የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የአረጋውያን፣ የአዕምሮ ሕሙማንና የሕጻናት መርጃ በጎ አድራጎት ማኅበር ተገኝቼ ነበር፡፡ ማኅበሩን የጀመረው በጎነት ነው፡፡ የተጀመረውም በ1999 ዓ.ም ነበር፡፡ ሲመሠረት አምስት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ይዞ በጥቂት ሰዎች ነበር የጀመረው፡፡ በዚህ ወቅት ግን 175 ደጋፊ ያጡ ዜጎችን አቅፏል፡፡ ይህ ማኅበር ጧሪ ያጡ አረጋውያንን ይንከባከባል፤ ጎዳና ላይ የወደቁ የአዕምሮ ሕሙማንን ያነሳል፤ ይንከባከባል፤ አሳዳጊ ያጡ ሕጻናትን ያሳድጋል፤ ያስተምራልም፡፡
የማኅበሩ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ብርሃን መልካሙ እንደተናገረው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በየሃይማኖት ተቋማቱ እየተዘዋወሩ በመለመን በሚያመጡት ይደጎማል፤ የከተማዋን ማኅበረሰብ ጨምሮ በገጠሩ ክፍል ዕርዳታ በመጠየቅ፣ የመንግሥት ሠራተኞች በየወሩ በሚያዋጧት ጥቂት መዋጮ ይተዳደራል፡፡
በማኅበሩ ውስጥ ያገኘናቸው እማሆይ ዝይን ፈረደ እነዚያ በጎ ሰዎች ከከፋ ሕይወት እንዳዳኗቸው ነግረውናል፡፡ እማሆይ ልጅ የላቸውም፡፡ ወደ ማኅበሩ ከመግባታቸው አስቀድሞ ሲበረቱ እየሠሩ ሲደክሙ ደግሞ እየለመኑ ይኖሩ ነበር፡፡ ቆይቶ ግን ለመለመንም ለመሥራትም የሚሆን አቅም አጥተው ያለ አስታማሚ ታምመው ተኙ፡፡ በዚህ የጭንቅ ሰዓት ነው በጎ ፈቃደኞቹ አግኝተዋቸው ወደ ማኅበሩ ያስገቧቸው፡፡ በቃሬዛ ገብተው እንደነበር የነገሩን እማሆይ ዝይን ማኅበሩ አሳክሞ፣ ተንከባክቦና ደግፎ ወደጤንነታቸው እንዲመለሱ እንዳደረጋቸው ነግረውናል፡፡ መልካም ልብ እንጂ መወለድ ቋንቋ መሆኑንም ነግረውናል፡፡ ‘‘እኛ ተመችቶናል እነርሱ ግን እየደከሙና እየለመኑ ነው የሚያጎርሱን’’ ነበር ያሉት እማሆይ፡፡
በ2009ዓ.ም ወደ ማኅበሩ እንደመጣ የነገረን በጎ ፈቃደኛው ቀናው ፀጋው ‘‘እንዲሁ ስጎበኝ ሁኔታቸው አሳዘነኝ፤ እነርሱም ወደው አይደለም እንዲህ የሆኑት ነገም እንደዚህ ላለመሆኔ ምንም ዓይነት ዋስትና የለኝም፡፡ እነርሱን ሳገለገል አላፊ የሆነውን ሁሉ አየዋለሁ፡፡ ስለሁሉም ነገር በፈጣሪ ዘንድ ዋጋ አገኝበታለሁ፡፡ ለአዕምሮዬም ደስታ ይሰማዋል፡፡ በእነርሱ ላይ ራሴን አያለሁ፡፡ ሌሎችም ወደዚህ መጥተው ቢያገለግሉ ከደካሞች ታላቅ ፀጋ አለ፡፡ ከዚያ ፀጋ መካፈል መልካም ነው፡፡” ነው ያለን፡፡ የአካባቢው ኅብረተሰብ ሳይሰስት ዕርዳታ እንደሚሰጥ የነገረን ፀጋው መጥቶ የመጎብኘት ችግር ግን መኖሩን ተናግሯል፡፡ በማኅበሩ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ደግሞ በየቀኑ ሰው ማዬትን እና መጫዎትን ይሻሉ፡፡ እረጅ ብቻ ሳይሆን ለጥቂት ሰዓት ቁጭ ብሎ የሚያወጋቸው ሰውም ይፈልጋሉ፡፡ የሚችል ሁሉ ይኼን ማድረግ ቢችል መልካም እንደሆነም ተናግሯል፡፡
በማኅበሩ ውስጥ 15 ያክል በጎ አፈቃደኛ ወጣቶች እንደሚገኙ ሥራ አስኪያጁ ነግረውናል፡፡ በጎ ፈቃደኞቹም ምግብ ከማሳባሰብ ጀምሮ፣ አብስሎ በመመገብ፣ ልብስ በማጠብ፣ ወደ ሕክምና በመውሰድ፣ መኝታቸውን በማጽዳትና ሙሉ እንክብካቤ በመስጠት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ናቸው፡፡ ይህ የበጎ ሐሳብና ድርጊት ማኅበር ቋሚ የሆነ ረጅና ሀብት ስለሌለው ችግር ላይ ነው፡፡ ከሁሉም ቀዳሚው የቀለብ አቅርቦቱ በሚፈለገው ልክ አለመሆኑ ነው፡፡ የውኃ፣ የአልጋ እና የመብራት ችግሮች አሉባቸው፡፡ የሚያገኙትን እህል የሚያስፈጩበትና የገቢ ምንጭም ሊሆናቸው የሚችል ወፍጮ እንደሚያስፈልጋቸውም ሥራ አስኪያጁ ነግረውናል፡፡
በኪራይ ቤት የጀመረው ይህ ማኅበር ወረዳው ቦታ ሰጥቶት አሁን ላይ በተሰጣቸው ስፍራ መኖር ቢጀምሩም የቤቱ ደረጃ ሌላ ፈተና ሆኗል፡፡ ሰው የሆነና መልካም ነገርን ማድረግ የሚፈልግ ሁሉ እንዲረዳቸው የጠየቁት ሥራ አስኪያጁ ብርሃን መልካሙ መንግሥትም ለማኅበሩ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ምክትል ዋና አስተዳደሪ ይርጋ ዓይቸው የገቢ ማሳባሰቢያ ፕሮግራም አቋቁመው እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ ግን ለአረጋውያኑ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሠራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን ለማኅበሩ የአልባሳት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል፡፡ በተለይም አንገብጋቢውን የምግብ ድጋፍ ለማድረግ እየሠሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገለጻ በክልሉ 155 ሺህ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ 88 ሺህ የሚሆኑት በአፋጣኝ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡