በጀትን በአግባቡ በመጠቀም ልማትን ለማፋጠን የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል፡፡

46

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የክልሉን የ2017 በጀት ዓመት የስምንት ወራት የበጀት አጠቃቀምን ከመሥሪያ ቤቶች ጋር ገምግሟል፡፡ የበጀት አጠቃቀሙ ከጊዜ ጊዜ እየተሻሻለ ቢኾንም ውስንነቶች መኖራቸው በግምገማው ተመላክቷል፡፡ ውስንነቶች እንዲስተካከሉም ቀነ ገደብ ተቆርጦ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የመደበኛ በጀት አፈጻጸም ጥሩ የሚባል ቢኾንም የካፒታል ፕሮጀክቶች በጀት አጠቃቀምም 25 በመቶ ብቻ እንደኾነ ተጠቅሷል፡፡ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንም በውይይቱ የተቀመጡ አቅጣጫዎች የት እንደደረሱ ለማሳወቅ ከቢሮው ምክትል ኀላፊ አታላይ ጥላሁን ማብራሪያ ጠይቋል፡፡

በጀት ለሚከናወኑ ሥራዎች ማስፈጸሚያ የሚመደብ ሀብት መኾኑን የገለጹት አቶ አታላይ ይህንን ውስን ሀብት በአግባቡ ተጠቅሞ ለማልማት የባለድርሻ አካላትም ኀላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ የክልሉ በጀት ከፌዴራል መንግሥት ድጎማ፣ ከከልሉ የሚሰበሰብ ገቢ እና ከውጪ እርዳታ እና ብድር የሚገኝ መኾኑን የጠቀሱት ምክትል ኀላፊው የበጀቱ 22 በመቶ ለክልል ቢሮዎች፣ 75 በመቶ ለታችኞቹ እርከኖች እና ቀሪው ለመጠባበቂ መመደቡን ተናግረዋል፡፡

ከአጠቃላይ በጀቱም 33 በመቶ ለካፒታል እና 67 በመቶ ለመደበኛ አገልግሎት መመደቡን ጠቅሰዋል፡፡ ቢሮውም በጀቱ ለተመደበለት ዓላማ እንዲውል ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የበጀት አጠቃቀም በታቀደው ልክ ካልኾነ እና አጠቃቀሙ በአግባቡ ካልተመዘገበ የበጀት አጠቃቀም ችግር እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ በጀትን በታቀደው ልክ አለመጠቀምም ሥራ አለመሥራት መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሥራ ተሠራ ለማለት ግን በጀትን ማጥፋት አይገባም ነው ያሉት።

በሥራ ማስኬጃ በጀት ሥራው በታቀደው ልክ ሳይፈጸም አስቀድሞ የመጠቀም፤ የካፒታል በጀት ላይ ደግሞ በጀቱ ጥቅም ላይ ሳይውል የመቅረት ዝንባሌዎች ይታያሉ፡፡ ይህም የበጀት አጠቃቀም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው ብለዋል፡፡ ይህንን ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ አስገዳጅ እርምጃዎች እየወሰድን ነው ያሉት አቶ አታላይ ምዝገባ በማያደርጉ ተቋማት ላይ የወጪ መርጃቸውን እስከ መከልከል ድረስ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የፋይናንስ ተቋማት እና መሪዎች ለበጀት አሥተዳደር ትኩረት እንዲሰጡ በመደረጉ የ2017 በጀት ዓመት የበጀት አሥተዳደር ከ2016ቱ መሻሻሉን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ የሚፈጸሙ የካፒታል ፕሮጀክቶችም በተቀናጀ የበጀት እና የወጪ አሥተዳደር ሥርዓት (አይቤክስ) ኮድ ተበጅቶላቸው እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሥራው ተሠርቶ እና ግዢው ተፈጽሞ ክፍያ ያለመፈጸም ወይም በአይቤክስ ያለመመዝገብ ውስንነቶች እንዳሉም በበጀት ግምገማው ተነስቷል፡፡ ይህንንም ለማስተካከል የተሰጠው የ15 ቀናት የጊዜ ገደብ ምን ለውጥ አመጣ ? ሲል አሚኮ ላነሳው ጥያቄ በክልሉ በነበረው የምክክር ኮሚሽን እና ሌሎች ሥራዎች መጠመድ ስላለ እንዲራዘም መጠየቁን ገልጸዋል፡፡ ያም ኾኖ በግምገማው አዎንታዊ ግብረ መልሶች መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ለበጀት አሥተዳደር የነበረው የትኩረት ማነስ ከግምገማው በኋላ እየተስተካከለ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የገንዘብ ቢሮ እና በየደረጃው ያሉ ተቋማት በጀትን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ሥልጠና በመስጠት እና ክትትል እያደረግን ነው ብለዋል፡፡ ለብክነት ተጋላጭ በጀቶችን በዓላማ እንዲገደቡ እንደተደረገም ጠቅሰዋል፡፡ የደመወዝ በጀትን ወደሌላ እንዳይዛወር መከልከሉንም በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡

በጀትን በአግባቡ በመጠቀም በኩል ሁሉም ኀላፊነት አለበት ያሉት አቶ አታላይ ኀላፊዎች፣ የውስጥ ኦዲተር፣ የግዥ ፣፣ ክፍያ ክፍል እና ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትም ኀላፊነት እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡ የበጀት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ግኝቶችን ለማስተካከልም በአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ያልታቀደ ግዢ መፈጸም እና የተጋነነ ወጪ ምን ይመስላል በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄም ችግሮች የነበሩ ቢኾንም የግዥ ሥርዓቱ ከጊዜ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ የበጀት አጠቃቀም ችግሩን ለመቀነስ የወጪ አፈጻጸምን (ላይን አይተም በጀቲንግ) መሠረት ካደረገ የበጀት አጠቃቀም ወደ ውጤትን ማዕከል ወደአደረገ የበጀት አሥተዳደር (ፕሮግራም በጀቲንግ) ሥርዓት ለመሸጋገር ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ሥርዓት ነዳጅ ያስፈልገኛል ብቻ ሳይሆን ነዳጅ ተጠቅሜ ምን ውጤት አመጣለሁ ብሎ ማቀድንም ይጠይቃል፡፡ በጀት የመጠቀምን ብቻ ሳይሆን ምን ውጤት እንደተገኘ የሚገልጽ ሪፖርትንም የሚጠይቅ ስልት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በሙከራ ትግበራ ጥንካሬ እና ድክመቶችን ተዳስሰው በ2019 ዓ.ም ወደ ሥራ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የሁሉም ዜጎች ተሳትፎ የበጀት አሥተዳደሩን ሥርዓት ውጤታማ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ችግሮችን በመፍታት እና ሁሉም በኀላፊነት እንዲሠራ በማድረግ ውጤታማ የበጀት አጠቃቀም እንዲኖር እናደርጋለን ብለዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበመልካም አስተሳሰብ እና ተግባር ብቁ የኾኑ መሪዎችን እና አባላትን ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።
Next articleየኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በፖፕ ፍራንሲስ ሕልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ።