መጤ እና ወራሪ አረሞች የግብርናው ዘርፍ ፈተና ኾነዋል።

34

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በየብስ እና በውኃማ አካላት ላይ የሚታዩ አረሞች መደበኛ፣ አደገኛ፣ መጤ እና ወራሪ ተብለው እንደሚመደቡ የዘርፍ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ መደበኛ አረም እንክብካቤ ባልተደረገለት ሰብል ውስጥ በመስፋፋት በምርታማነት ላይ ጉዳት የሚያደርስ አርም ነው። አደገኛ፣ መጤ እና ወራሪ አረሞች ደግሞ በእንስሳት፣ በወራጅ ውኃ እና የከብቶች ፍግ ለኮምፖስት ሥራ በሚውልበት ወቅት በመሳሰሉ አስተላላፊ መንገዶች በቀላሉ የሚተላለፍ ናቸው።

አረሞቹ በዓይነት፣ በመጠን እና በተስፋፊነት ፍጥነታቸው ከፍተኛ በመኾናቸው በምርታማነት ላይ የሚያደርሱት ጉዳትም በዚያው መጠን ከፍተኛ ነው። አሁን ላይ በውኃማ አካላት፣ በእርሻ እና በግጦሽ ቦታዎች አድማሳቸውን እያሰፉ ይገኛሉ። የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚም እየፈተኑት ከሚገኙ ችግሮች መካከልም የሚመደቡ ናቸው።

የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ እና የአየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ ባለሙያ አወቀ ይታይ መደበኛ አረም በግብርና ቢሮ ኀላፊነት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። መጤ እና ተስፋፊ አረሞች በአካባቢ እና በማኅበረሰቡ ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት አኳያ አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። እስከ አሁን በአማራ ክልል 12 የሚኾኑ አደገኛ፣ መጤ እና ተስፋፊ አረሞች የተለዩ ሲኾን 740 ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ በወራሪ አረም መሸፈኑን ተናግረዋል።

እነዚህ አረሞች ይበልጥ በምሥራቁ የክልሉ ክፍል በስፋት ተስፋፍተው የሚገኙ ቢኾንም አሁን ላይ ወደ ምዕራቡ የአማራ ክፍልም እየተስፋፉ ይገኛሉ ነው ያሉት። በምርታማነት ላይ የመጠን እና የጥራት ማጓደል እያስከተሉ ይገኛሉ ብለዋል። አቀንጭራ የተባለው አደገኛ አረም 65 በመቶ፣ የቅንጨ አረም ደግሞ 15 በመቶ የምርት መቀነስ እንደሚያስከትልም ለአብነት አንስተዋል።

አረሞቹ ድርቅ እና ውርጭን የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛ በመኾኑ እጽዋት በቀላሉ እንዳይራቡ፣ እንዳይለመልሙ እና ምርት እንዳይሰጡ የማድረግ አቅማቸው ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡ የግጦሽ መሬትን ያመናምናሉ፤ አረሙን ከብቶች በሚመገቡበት ወቅት የወተት፣ የሥጋ ጣዕም እና ጥራት መጓደል ያመጣሉ ነው ያሉት፡፡ የማር ምርትን ጣዕም እንደሚቀንሱም ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮች በሚያርሙበት ወቅት የቆዳ ማሳከክ፣ ማሳበጥ፣ መሰንጠቅ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ሽታ ስላላቸው ለአስም እና መሰል ሕመሞች እንደሚያጋልጡም ገልጸዋል። ባለሙያው እንዳሉት የአረሙን ሥርጭት ለመከላከል በየጊዜው የማስወገድ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። በ2017 ዓ.ም ለማስወገድ በእቅድ ከተያዘው 180 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ በዘጠኝ ወሩ 146 ሺህ ሄክታሩን ማስወገድ መቻሉን በማሳያነት አንስተዋል።

በአረሙ አወጋገድ እና ቁጥጥር ላይ አሁን ላይ እየወጡ በሚገኙ ሕጎችም ጭምር ትኩረት እንዲሰጠው እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የወራሪ እና መጤ ዝርያዎች ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ ወንድምነው አብሬ በኢትዮጵያ ከ35 በላይ የሚኾኑ ወራሪ እና መጤ ዝርያዎች ተለይተዋል ብለዋል። ከ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ደግሞ በአረሙ ተወርሯል ነው ያሉት።

ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ፕርፕሮሶፒስ( የወያኔ ዛፍ) ፣ ፓርቲኒየም፣ እምቦጭ እና የወፍ ቆሎ ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል። ፕርፕሮሶፒስ( የወያኔ ዛፍ) እየተባለ የሚጠራው አረም በአፋር፣ በሶማሌ እና በአማራ ክልሎች በስፋት ተሠራጭቶ ይገኛል ነው ያሉት። የወፍ ቆሎ እና ፓርቲኒየም በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በስፋት ተንሰራፍቶ ይገኛልም ብለዋል።

ተስፋፊ አረሞቹ በግድቦች፣ በሐይቆች እና በወንዞች ላይም ከፍተኛ የኾነ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉ ነው ያሉት። በተለይም ደግሞ እምቦጭ በሀገሪቱ በሚገኙ እንደ ጣና፣ ዝዋይ፣ ቆቃ፣ አባያ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በጋምቤላ በሚገኙ ሐይቆች እና ወንዞች ላይ በመስፋፋት በዓሳ እና ሌሎች ሀብቶች ላይ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ ብለዋል።

ባለሥልጣኑ የአረም ዝርያዎቹ በየብስ እና በውኃማ አካላት ላይ እያደረሱት ያለውን ጉዳት ለመቀነስ በሰው ጉልበት እና በማሽን የማስወገድ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በ2017 ዓ.ም 400 ሺህ ሄክታር መሬት ወራሪ እና መጤ ዝርያዎችን ለማስወገድ ታቅዶ በስድስት ወሩ 243 ሺህ ሄክታር መሬት አረም መወገዱን ነው የገለጹት።

ወራሪ አረሞችን ለመከታተል እና ለመቆጣጠር በሀገር አቀፍ ደረጃ ስትራቴጅ ተዘጋጅቷል ብለዋል። ስትራቴጅው በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2030 ከፖሊሲ አውጭው እስከ ማኅበረሰቡ ድረስ ስለ አረሙ ግንዛቤ ማሳደግ አላማ ያደረገ እንደኾነ ገልጸዋል።

በ2050 ደግሞ የወራሪ እና መጤ አረም ዝርያዎች በአካባቢ፣ በብዝኃ ሕይዎት እና በሥነ ምህዳር ላይ የሚያደርሱትን ተጽዕኖ መቀነስ ላይ ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት።

በቀጣይ ባለሥልጣኑ ለስትራቴጅው ማስፈጸሚያ የሚኾኑ የሕግ ማዕቀፎችን እና መመሪያ ማኑዋሎችን የማዘጋጀት ሥራዎችን እንደሚሠራም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመኖሪያ ቤት ኪራይ እና ሕጉ!
Next articleበመልካም አስተሳሰብ እና ተግባር ብቁ የኾኑ መሪዎችን እና አባላትን ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።