የመኖሪያ ቤት ኪራይ እና ሕጉ!

112

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አዋጅ ቁጥር 1320/2016 የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አሥተዳደርን የተመለከተ የሕግ ማዕቀፍ ነው። ዓላማውም በመኖሪያ ቤት እጥረት እና በመኖሪያ ቤት ኪራይ መናር የሚከሰተውን የኑሮ ውድነት ጫና በመቀነስ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋን ከተከራዮች አቅም ጋር የተመጣጠነ እንዲኾን ዓላማ አድርጎ የተደነገገ ነው።

አቶ ደመቀ ይብሬ በአማራ ሚዲያ ኮርፓሬሽን የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ ናቸው። ከዚህ በፊት የመኖሪያ ቤት ኪራይ በፍታብሔር ሕጉ ሲመራ የነበር ነው ብለዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት እና የመኖሪያ ቤት ኪራይ መናርን አስመልክቶ የአከራይ እና የተከራይ ሚዛናዊነትን ለማስጠበቅ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1320/2016 በሚል አዋጅ እንዲደነገግ ተደርጓል ይላሉ።

እዚሁ አዋጅ ላይ አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ እንደተቀመጠው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ማለት ለመኖሪያነት የሚያገለግል አንድ ወይም ከአንድ በላይ ክፍሎችን የያዘ ቤትን ተከራይ ለሚያገኘው አገልግሎት ለአከራዩ ክፍያ የሚፈጽምበት ሂደት እንደኾነ በአዋጁ ተደንግጓል ነው ያሉት። አዲሱ አዋጅ የተፈጻሚነት ወሰኑ በአንቀጽ ሦስት ላይ የተመለከተ ነው። አዋጁ ተፈጻሚ የሚኾነው ለክልል ተጠሪ የኾኑ ከተሞችን ወይም ሜትሮ ፖሊታንት ከተሞችን የሚመለከት ኾኖ የወጣ እንደኾነ አቶ ደመቀ ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች ላይ በሚፈጸም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ላይ ተፈጻሚ እንደሚኾንም ለይቶ አስቀምጧል ነው ያሉት። ሌሎች በክልል ስር የሚገኙ ከተሞችን በተመለከተ ግን አዋጁ ተፈጻሚ የሚኾንበትን ሁኔታ ክልሎች ነባራዊ ሁኔታቸውን ታሳቢ በማድረግ ሊወስኑ እንደሚችሉ ተደንግጓል ብለዋል።

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ግንኙነት ተፈጻሚ የሚኾነው በመኖሪያ ቤት ነው ካልን ይላሉ አቶ ደመቀ ሌሎች ተፈጻሚ የማይኾኑባቸው ነገሮችም አሉ ማለት ነው ብለዋል። ይህም አዋጁ ሆቴሎችን፣ ሪዞርቶችን፣ እንግዳ ማረፊያዎችን፣ በንግድ ፈቃድ መሠረት የሚከራዩ ቤቶች ላይ አዋጁ ተፈጻሚ አይኾንም ነው ያሉት።

የመኖሪያ ቤት ውል እና ምዝገባን በተመለከተ ማንኛውም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል በጽሑፍ መደረግ እንዳለበት በአዋጁ ተደንግጓል ብለዋል። በጽሑፍ ብቻም ሳይኾን አከራዩ እና ተከራዩ በተፈራረሙ በ30 ቀናት ውስጥ ለተቆጣጣሪው አካል ቀርቦ መመዝገብ እንዳለበትም አዋጁ ያስረዳል ነው ያሉት።

ወይም ሠነድ ለማረጋገጥ ሥልጣን በተሰጣቸው አካላት ላይ ቀርቦ መመዝገብ ይኖርበታል ብለዋል። ሲመዘገብም አከራይ እና ተከራይ ወይም ወኪሎቻቸው በተገኙበት መመዝገብ ይኖርበታል ነው ያሉት። ውል የማረጋገጥ ግዴታውን ያልተወጣ አከራይ ወይም ተከራይ በኪራይ ውሉ ላይ ያለው የቤቱ የኪራይ ዋጋን የሦስት ወር ኪራይ ያልበለጠ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጠየቅም በአዋጁ በግልጽ ተቀምጧል ብለዋል አቶ ደመቀ።

የኪራይ ውል ዘመንን በተመለከተ ደግሞ ከሁለት ዓመት ያነሰ ሊኾን እንደማይችል ተቀምጧል ይላሉ። ይህም አከራይ ተከራይን በፈለገው ጊዜ እንዳያስወጣው በማሰብ ነው። ሁለት ዓመት በአከራይ ተከራይ ሕጉ ዝቅተኛው የውል ዘመን ነው ብለዋል። በሽያጭ፣ በውርስ እና በሌሎች ምክንያቶች ቤቱ ለሌላ ሦስተኛ ወገን ከተላለፈ ውሉ ሊቋረጥ የሚችለው አከራዩ ለተከራዩ የስድስት ወር ማስጠንቀቂያ ቀድሞ ከነገረው ብቻ ነው ብለዋል። ከዚያ ውጭ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ውጣ ማለት አይቻልም ነው ያሉት።

ነገር ግን የኪራይ ዘመኑ አልቆም ከተግባቡ ውሉን አድሰው ሊቀጥሉ ይችላሉ ብለዋል። ስለዚህ የውል ዘመኑ ሳይጠናቀቅ ማስወጣትም ኾነ ዋጋ መጨመር በሕግ የሚያስጠይቅ ይኾናል ነው ያሉት። ይሁንና ይላሉ አቶ ደመቀ ውሉ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ያለ ቢኾንም አከራይ እና ተከራይ ከተስማሙ የገቡትን ውል በስምምነት ማቋረጥ እንደሚችሉ ተቀምጧል ብለዋል።

የአከራይ ተከራይ ውሉ ከሁለት ዓመት በላይ እንዲኾን የተደረገው ተከራይን ከእንግልት ለመታደግ እና በፈለገው ጊዜ ውጣ የሚባለውን የተከራይ እንግልት ለማስቀረት ታስቦ እንደኾንም አንስተዋል። በአከራይ ተከራይ አዋጁ 1320/2016 መሠረት መብት እና ግዴታዎች በግልጽ የተቀመጡ ናቸው። አከራይ የውል ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት የኪራይ ዋጋ መጨመር እና ሕጉ ከሚፈቅደው ሥርዓት ውጭ ማስወጣት አይችልም። ምናልባትም ተቆጣጣሪው አካል የኪራይ ማስተካከያ ዋጋ ካደረገ ብቻ ለውጥ ሊኖር ይችላል ነው ያሉት።

ሌላው የአከራይ ግዴታ ተብሎ በአዋጁ የተቀመጠው አከራዩ ቤቱን ለሦስተኛ ወገን የሚያስተላልፈው ከኾነ ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ ስድስት ወር ቀድሞ ለተከራዩ የማሳወቅ ግዴታ አለበት ብለዋል። ቅድመ ክፍያን በተመለከተ ደግሞ ከሁለት ወር በላይ ቅድመ ክፍያ ከተከራዩ መቀበል በሕግ ያስጠይቃል ነው ያሉት።

የቤት ኪራይ ክፍያ ሰነዶችን በሚገባ አደራጅቶ መቀመጥም የአከራይ አንዱ ግዴታ እንደኾነ አብራርተዋል። ሌላው የቤት ኪራይ ክፍያ መፈጸም ያለበት በባንክ ወይም በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ዘዴዎች እንደኾነ በአዋጁ እንደተቀመጠ አቶ ደመቀ ተንትነዋል። ከዚያ ውጭ ባሉ የክፍያ መንገዶች ምሳሌ በካሽ መክፈል እንደማይቻልም አዋጁ ደንግጓል ነው ያሉት.። እነዚህን የክፍያ መረጃዎችን መያዝ የአከራዩ ግዴታ ነው ብለዋል።

የተከራይ ግዴታ ብለው ያነሱት ለአብነት ወቅቱን ጠብቆ ክፍያ መስጠት የተከራዩ ግደታ ነው ብለዋል። ሌላው ቤቱን በፈቃዱ መልቀቅ ሲያስብ የሁለት ወር ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ለአከራዩ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት በአዋጁ ተገልጿል ብለዋል። ልክ እንደ አከራዩ ሁሉ የተከራይ ውሉን ያሟላ ወይም ያስመዘገበ መኾንም የተከራይ ግዴታ ነው ብለዋል።

አከራይም ኾነ ተከራይ በዕለት ከዕለት የአብሮነት ኑሯቸው የወንጀል ሥራ ከሠሩ እንደ ወንጀሉ አይነት ታይቶ በወንጀል ሕጉም ሊጠየቁ ይችላሉ ነው ያሉት። የኪራይ ሕጉን ካለማክበር ጋር የተያያዙ ነገሮች ካሉ ከሦስት ወር ባልበለጠ ቤቱ ሊያወጣ የነበረውን የኪራይ ዋጋ እንደሚጠየቁ አዋጁ ማስቀመጡን አቶ ደመቀ ተናግረዋል። ይህ አፈጻጸምም ለአከራዩም ኾነ ለተከራዩ የሚሠራ ይኾናል ብለዋል።

“ልማድ ሕግ ሊኾን አይችልም” የሚሉት አቶ ደመቀ እንደ ማኅበረሰብ እስከ አሁን እየተጠቀምንበት ያለው የአከራይ ተከራይ ልምድ አዲስ ከወጣው አዋጅ አንጻር መሻሻል ያለበት ነው ባይ ናቸው። ለዚህም ሰፊ ጥረት እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ሊከናወን እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሌላው አዲስ ከወጣው የአከራይ ተከራይ ሕግ አንጻር ቀደም ሲል ሲከራይ የነበረ መኖሪያ ቤት ወይም አዲስ የተገነባ ቤት አገልግሎት ሳይሰጥ ወይም ሳይከራይ ከስድስት ወር በላይ ከተቀመጠ ቤቱ ቢከረይ ኖሮ ሊያወጣ የሚችለው ገንዘብ ተሰልቶ የገቢ ግብር መክፈል እንዳለበት ተደንግጓል ብለዋል።

የቤት ኪራይ ውል በሁለት መንገድ ሊቋረጥ ይችላል፤ በማስጠንቀቂያ እና ያለ ማስጠንቀቂያ። ማስጠንቀቂያ አከራይም ኾነ ተከራይ በኾነ ምክንያት እስከዚህ ጊዜ ልቀቅልኝ ወይም እለቃለሁ ተባብለው የሚነጋገሩበት ነው።

ያለ ማስጠንቀቂያ ደግሞ ተከራዩ በውል የጊዜ ገደቡ መሠረት የማይከፍል ከኾነ፤ የኸውም ለመጀመሪያ ጊዜ 15 ቀን ያሳለፈ ከኾነ ለሁለተኛ ጊዜ ከኾነ ደግሞ ሰባት ቀን ካሳለፈ ያለ ማስጠንቀቂያ ውሉን ማቋረጥ እንደሚችል በአዋጁ ተቀምጧል ብለዋል አቶ ደመቀ።

ከዚህ በተጨማሪ ያለ አከራዩ ፈቃድ ቤቱ ከመኖሪያነት ውጭ ሌሎች ተግባራትን ምሳሌ ንግድ ከሠራበት ውሉ ያለማስጠንቀቂያ ሊቋረጥ ይችላል ብለዋል። በሌላ መንገድ የአካባቢውን ሰላም ሊያውክ በሚችል መንገድ ተከራዩ ቤቱን የሚጠቀምበት ከኾነም ያለማስጠንቀቂያ ውሉን ሊያቋርጥ ይችላል ነው ያሉት።

ሌላው አስቦም ኾነ በቸልታ በተከራየው ቤት ላይ ጉልህ ጉዳት ካደረሰበትም ውሉ ይቋረጣል ብለዋል።

ባጠቃላይ ለጋራ ተጠቃሚነት ሲባል አከራዮችም ኾነ ተከራዮች የውል ምዝገባ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፤ አከራይም ኾነ ተከራይ ተገቢ ሰነዶችን በሚገባ መያዝ አለባቸው፤ የአከራይም ኾነ የተከራይ መታወቂያ እና የቤቱ ካርታ መኖር አለበት ነው ያሉት።

ይህ ሳይኾን ቀርቶ ከሁለቱ አንዱ ከአሠራር ቢወጡ ችግሩ በተፈጠረ በ30 ቀናት ውስጥ ለተቆጣጣሪው አካል ማሳወቅ እንደሚችሉም አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጠል አስታወቀ።
Next articleመጤ እና ወራሪ አረሞች የግብርናው ዘርፍ ፈተና ኾነዋል።