
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከወቅታዊ የኢትዮጵያና ግብፅ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውዝግብ ዙሪያ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የዓለማቀፍ ሕግ መምህር ዘውዱ መንገሻ ቀጣዩን ጽሑፍ አድርሰውናል፡፡
ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው አቤቱታ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመሥረቻ ቻርተር አንጻር፡፡
ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሠራርና የውኃ አሞላል ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አለመግባባት መሠረት በማድረግ አቤቱታ ማቅረቧ ከሰሞኑ ተሰምቷል፡፡ ‘‘ለመሆኑ ግብፅ ለፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው አቤቱታን ተመልክቶ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትልቁ የስልጣን ባለቤት ምን ሊወስን ይችል ይሆን? ጉዳዩን ተቀብሎ ለማየት ስልጣንን አለውን? ኢትዮጵያስ ምን ማድረግ ይኖርባታል?’’ የሚሉ ጉዳዮች ከሰሞኑ የብዙዎችን ትኩረት ስበዋል፡፡ ለመሆኑ የፀጥታው ምክር ቤት ግብፅ ያቀረብችውን አቤቱታ የሚያይበት ስልጣን አለውን? ምንስ ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል? ውሳኔው ሀገራቱን ያስገድዳቸዋልን? በ1945 (እ.አ.አ) የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመሥረቻ ቻርተር በምዕራፍ 6 አንቀፅ 33 ላይ ‘‘ሀገራት ያሉባቸውን አለመግባባቶች ሁሉ ሰላማዊ በሆኑ የግጭት አፈታት መንገዶች ሊፈቱ ይገባል’’ ይላል፡፡ ሀገራት ለፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች ከሌላ ሀገራት በሚገጥሟቸው ጊዜ በጉዳዩ ላይ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲሰጥበት ለፀጥታው ምክር ቤት ወይም ለጠቅላላው ጉባኤ ማመልከት እንደሚችሉ በአንቀፅ 35 ላይ ተገልጿል፡፡ ግብፅ በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አለመግባባት ለፀጥታ መደፍረስ መንስኤ ሊሆን ይችላል በሚል መንፈስ ለፀጥታው ምክር ቤት የወቅቱ ሰብሳቢ ኢስቶንያ እንዲቀርብ አድርጋለች ነው፡፡ ይህንን አቤቱታ ተከትሎ የፀጥታው ምክር ቤት ምን ሊያደርግ ይችላል? የሚለው ሌላው ነጥብ ነው፡፡
የምክር ቤቱ አባል ሀገራት የቀረበውን ጉዳይ ለፀጥታ መደፍረስ መንስኤ ሊሆን ይችላል ወይም አይችልም በሚለው ዙሪያ ውይይት በማድረግ ‘‘ለፀጥታ መደፍረስ መንስኤ ነው ወይም አይደለም’’ የሚል ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ ላይ ኢትዮጵያ በተገቢው መጠን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በማድረግ በአሁኑ ወቅት ያሉትን የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራትን ማለትም (ከአምስቱ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት በተጨማሪ ለቤልጅዬም፣ ጀርመን፣ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኒጀር፣ ሲንትቨንሰንት፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኢስቶንያ፣ ቬትናም እና ቱኒዝያ) ስለግድቡ ተገቢ መረጃ በመስጠትና ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት ከጀመረች አንስቶ እስካሁን ድረስ ከግብፅ ጋር በትብብር መንፈስ ያደረገቻቸውን ተግባራት በተገቢው ሁኔታ ማስረዳትና ወንዙን በመጠቀም የመልማት መብት እንዳለትም መግለጽ ይጠበቅባታል፡፡ በተፋሰሱ ውስጥ ያለውን የግብፅ ከፍተኛ የወንዙን አጠቃቀም ግልጽ ማድረግ፣ የኢትዮጵያ አቋም ተፈጥሯዊ የሆነና ባላት የተፈጥሮ ሀብት ላይ በፍትሐዊነትና በእኩልነት (የዓባይ ወንዝን ጨምሮ) የመጠቀም ጥያቄ እንደሆነ በግልፅ ማስረዳትና ጉዳዩ በውይይትና በድርድር ሂደት ላይ እያለ ግብፅ ከፕሮጀክቱ (ከግድቡ ውጭ) ያሉ ነገሮችን በማንሳት በቅኝ ግዛት ስምምነቶች አገኘሁ የምትለውን የውኃ ድርሻ በእጅ አዙር ኢትዮጵያ ዕውቅና እንድትሰጥ የሚደረግ ጥረት እንደሆነ ማጋለጥም ይኖርባታል፡፡
በአጠቃለይ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብት መሠረት ያደረገ ጥያቄ እንጂ ወደ ፀጥታ መደፍረስ የሚያስኬድ ጉዳይ አይደለም በሚል የፀጥታ ምክር ቤት አባል ሀገራት አቋም እንዲይዙና ውሳኔ እንዲያሳርፉበት ማድረግ ይገባታል፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን በኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴና ማድረግ፣ የዲፕሎማሲ እና የዓለም አቀፍ ውኃ ሕግ ባለሙያዎችንም በተገቢው ሁኔታ አስተባብሮ መጠቀምና የጎላ ርብርብ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህም ጥረት በግብፅ በ15 ገፆች ተደግፎ የቀረበውን አቤቱታ በአግባቡ ማክሸፍ የሚችል እና የግብፅን ተንኮልና ደባ በአግባቡ የሚሣይ ሊሆን ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን ማድረግ ካልቻለችና ግብፅ ያላትን የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ በመጠቀም የፀጥታው ምክር ቤት አባላት የቀረበውን ጉዳይ ‘‘የሀገራቱን ፀጥታና ደኅንነት የሚመለከት ነው’’ የሚል ውሳኔ እንዲሰጥ ማድረግ ከተቻላት በቀጣይ ምክር ቤቱ ‘‘ሀገራቱ ምን ሊያደርጉ ይገባል?’’ የሚለውን አጀንዳ በማንሳት በ15ቱ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት መካከል ውይይት ይደረግበታል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ላይ የፀጥታው ምክር ቤት ውይይት በማድረግ ‘‘ሀገራቱ የገጠማቸው አለመግባባት በምን ዓይነት መንገድ ሊፈታ ይገባል?’’ በሚለው ዙሪያ የውሳኔ ሐሳብ ይሰጣል፡፡ ብዙ ጊዜ የሚሰጠው መፍትሔ ሀገራቱ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ በንግግርና በድርድር እንዲፈቱ የሚል መንፈስ ያለው ነው፡፡ ምናልባትም ምክር ቤቱ አንድም ሀገራቱ ሊከተሉት ስለሚገባ የግጭት አፈታት ሂደት የተለያዩ አማራጮችን ሊጠቀም ይችላል፡፡ ምክር ቤቱ ይህንን የውሳኔ ሐሳብ ሲሰጥ ሀገራቱ ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ ያለፉበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ እንደሚያስገባ በአንቀፅ 36 ላይ ተደንግጓል፡፡
ነገር ግን በምዕራፍ 6 መሠረት ለፀጥታው ምክር ቤት በሚቀርብ ጉዳይ ላይ ምክር ቤቱ የሚሰጠው የውሳኔ ሐሳብ ለሁለቱ ሀገራት ሙሉ ለሙሉ ተቀብለው የመተግበር ግዴታ አይጥልባቸውም፡፡ ምክንያቱም የቻርተሩ አንቀፅ 36 እንደሚደነግገው ለፀጥታው ምክር ቤት በዚህ ጉዳይ የተሰጠው ስልጣን አስገዳጅ ያልሆነ የመፍትሔ ሐሳብ መስጠት በመሆኑ ነው፡፡ ሀገራቱ የተሰጠውን ምክረ ሐሳብ ተቀብለው ለተግባራዊነቱ ከሠሩ እና ችግራቸውን ከፈቱ ጉዳዩ ከዚህ ላይ እልባት ያገኛል፤ ነገር ግን በተሰጠው ምክረ ሐሳብ ሁለቱ ሀገራት ጉዳዩን መፍታት ካልቻሉና ወደ ግልፅ ግጭት የሚያመሩ ከሆነ (በኔ እሳቤ ይህ ሊከሰት ይችላል ብዬ አላስብም) የፀጥታው ምክር ቤት በምዕራፍ 7 በተጠቀሰው መሠረት አስገዳጅ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ከዚህ ላይ የሚሰጠውን የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ሀገራት የማክበር ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህንን በማያከብር ሀገር ላይ ልዩ ልዩ ማዕቀቦች ሊጣልበትም ይችላል፡፡
ከዚህ ላይ መታየት ያለበት መሠረታዊ ነገር አንድ ሀገር የፀጥታው ምክር ቤት አስገዳጅ ያልሆነ ውሳኔ እንኳን ቢሆን ያንን ውሳኔ ያለመተግበር በሀገሪቱ ላይ የሚፈጥረው የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ያለው መሆኑ ነው፡፡ በሀገራቱ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይም ጉዳት ይኖረዋል፡፡
በመሆኑም በተቻለ መጠን በዚህ ወቅት የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት ጉዳዩን ከማየታቸው በፊት ስለጉዳዩ ተገቢ የሆነ መረጃ እንዲኖራቸው ለማስቻል ከኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ የዲፕሎማቲክ እንቅስቃሴ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡