
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በቬይትናም ያደረጉት ጉብኝት የሀገራቱን ግንኙነት የሚያጠናክር እና ተሞክሮ የተቀሰመበት መኾኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኀላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኀላፊ ቢልለኔ ስዩም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ባሳለፍነው ሳምንት በቬይትናም ያደረጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቬይትናም ቆይታቸው ከሀገሪቱ የተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር መምከራቸውን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም በሁለቱ ሀገራት መካከል በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችል ውይይት መደረጉን ነው ያብራሩት፡፡ የቬይትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን በቤተ መንግሥታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ደማቅ አቀባበል በማድረግ መወያየታቸውንም አንስተዋል፡፡
በውይይታቸውም በተለይም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትስስር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አብራርተዋል፡፡ ቬይትናም በብዛት የምትታወቀው መዋዕለ ንዋይ በመሳብ መኾኑን ጠቅሰው፤ ከሀገሪቱ በኢኮኖሚ፣ ኢንዱስትሪ፣ ግብርና እና ሌሎች ዘርፎች ተሞክሮ መቀሰሙን ገልጸዋል፡፡
ከሀገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በተደረጉ ውይይቶች በኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ግንኙነቱን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚፈልጉ መናገራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በአፍሪካ በኢነርጂው ዘርፍ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ኢንቨስትመንቶችን ማበረታታት እንደሚገባ ማንሳታቸውን ተናግረዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት በቀዳሚነት የምታደርገው ጥረት እና በአሕጉሪቱ መንጸባረቅ እንዳለበት መግለጻቸውን ኀላፊዋ አንስተዋል።
ሀገር በቀል የኾኑ እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መግታት የሚያስችሉ ኢንሼቲቮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ መጥቀሳቸውን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል በምታደርገው ግስጋሴ በጉብኝቱ ከቬይትናም ሰፊ ልምድ የቀሰመችበት፣ በግብርና በኢንዱስትሪ እና በሌሎች ዘርፎችም በርካታ ተሞክሮ የወሰደችበት እንደነበረም ገልጸዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የቬይትናም ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ባሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችል የሁለትዮች ምክክር የተደረገበት ነውም ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!